Search

በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ለትምህርት ጥራት እና ውጤታማነት መጠናከር ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል - የትምህርት ሚኒስቴር

እሑድ ሐምሌ 26, 2018 68

7ኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት ፕሮግራም (ESDP VII) ረቂቅ ዕቅድ ላይ ውይይት ማድረጉን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ የምክክር መድረክ ላይ በስትራቴጂያዊ ጉዳዮች የቀረበው 7ኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት ፕሮግራም (ESDP VII 2026/27 to 2030/31) ረቂቅ ዕቅድ፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የትምህርት ጥራትና ውጤታማነትን ማጠናከር ዋና ትኩረት እንደሚሆን አመላክቷል።

በረቂቅ ዕቅዱ መሠረት፣ የትምህርት ጥራትን እና ተገቢነትን ለማረጋገጥ ቀደም ሲል የተጀመሩ ሥራዎችን በአዳዲስ አሠራሮች ማጠናከር፣ የትምህርትን ውጤት በተጨባጭ መለካት እና በትምህርት ዘርፍ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ቅድሚያ የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።

ፕሮግራሙ አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት በውጤታማነት መተግበር፣ ምዘናን በብቃት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ፣ የተማሪዎችን የመማር ውጤት ማሻሻል እንዲሁም በቋንቋ፣ በሒሳብ እና በሳይንስ ትምህርቶች ያላቸውን ብቃት ማሳደግን እንደ ዋና ተግባራት አካቷል።

በተጨማሪም የዲጂታል ትምህርትን ማስፋፋት፣ የብሔራዊ ፈተናዎችን ማዘመን፣ በቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና (TVET) እና በከፍተኛ ትምህርት መካከል ያለውን ቅንጅት ማጠናከር፣ የመምህራንን ሙያዊ ብቃት እና ማበረታቻ ማሻሻል፣ እንዲሁም የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጆችን እና ዩኒቨርሲቲዎችን ማጠናከር በዕቅዱ ውስጥ ተካትተዋል።

ረቂቅ ዕቅዱ የትምህርት ጥራት፣ ተገቢነትን ተደራሽነትን እና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት የተጎዱ የትምህርት ማኅበረሰቦችን መልሶ ማቋቋም፣ ትምህርትን ሳይቋረጥ እንዲዘልቅ የሚያስችል ሥርዓት መገንባት፣ እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች እና የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ እና ውጤታማነት ማረጋገጥ ላይም ልዩ ትኩረት መስጠቱን ያመለክታል።

7ኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት ፕሮግራም (ESDP VII) ረቂቅ ዕቅድ በምክክር መድረኩ ላይ ቀርቦ፣ በክልል እና በከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም በዘርፉ ባለድርሻ አካላት ሰፊ ውይይት የተደረገበት መሆኑን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: