Search

የነገዋን ጠንካራ ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ የምክክር መድረኩ ታሪካዊ መሰረት እየጣለ ነው፡- የሀገራዊ ምክክር ተመካካሪዎች

ረቡዕ ሐምሌ 29, 2018 93

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር መድረክ ላይ የሚገኙ ተመካካሪዎች ወቅታዊው የምክክር ሂደት የነገዋን ጠንካራ፣ ሰላማዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ታሪካዊ አጋጣሚን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመካካሪዎቹ እንደሚያስረዱት በየአካባቢው የሚነሱ ልዩ ልዩ የልማትና የማህበራዊ ጥያቄዎችን እንዲሁም ሀገራዊ አጀንዳዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ በነጻነት ለመመካከር የመድረኩ መዘጋጀት ወሳኝ እርምጃ ነው።

ይህን ታሪካዊ እድል ያገኙ 4 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በሀገር ጉዳይ ላይ ለመምከርና ለመወሰን መቻላቸው ትልቅ እድል መሆኑን ጠቅሰው፣ መድረኩ የልዩ ልዩ ባህሎችና ቋንቋዎች ባለቤቶች እንዲተዋወቁና እንዲዋሃዱ አወንታዊ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ተመካካሪቹ "ማየት ማመን ነው" በማለት የመድረኩን ሂደት ያደነቁ ሲሆን፣ እናቶች፣ አባቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በትልቅ ሀገራዊ ተስፋ ሀሳባቸውን ሲያንሸራሽሩ ማየታቸው የወደፊቷን ዴሞክራሲያዊ እና እኩልነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይት ሂደቱን በተመለከተ ተሳታፊዎቹ በመድረኩ በርካታና የተቀራረቡ ሀሳቦች የሚነሱበት፣ ጥልቅ ክርክር የሚደረግበትና የጋራ ስምምነት የሚደረስባቸው ሂደቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ውይይቱ 10 ሰዎች ጀምሮ ደረጃ በደረጃ ወደ 50 250 እና አሁን ደግሞ ወደ 500 ተሳታፊዎች እያደገ የመጣና በየደረጃው ከህዝብ የመጡ ተወካዮች ጥልቅ ውይይት እያደረጉበት በመሆኑ አጠቃላይ ሂደቱ ለኢትዮጵያ የወደፊት በጎ እርምጃ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

ተመካካሪዎቹ እንደገለጹት እያንዳንዱ ተሳታፊ የራሱ የሆነ አመለካከትና ሀሳብ ቢኖረውም ውይይቱ ትኩረት የሚያደርገው ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ አንድነትና ህብረት በሚጠቅሙ ዋና ዋና ሀሳቦች ላይ ነው።

በተለይም የጋራ የሆኑ እሴቶችንና ሀሳቦችን በመለየት፣ ኢትዮጵያ በቀጣይ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የእድገት፣ የብልጽግና እና የሰላም ማሳያ እንድትሆን የማድረግ ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: