Search

ኢትዮጵያ የቡና በሽታን ለመለየትና ለማከም የሚያስችሉ አዳዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችን እና ምርምሮችን በማሳደግ ላይ ትገኛለች፦ የጠቅላይ ሚንስትር ፅሕፈት ቤት

እሑድ መስከረም 10, 2019 34

ኢትዮጵያ የቡና በሽታን ለመለየትና ለማከም የሚያስችሉ አዳዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂዎችን እና ምርምሮችን በማሳደግ ላይ እንደምትገኝ የጠቅላይ ሚንስትር ፅሕፈት ቤት አስታወቀ።

ፅሕፈት ቤቱ "ቡና ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ስጦታ መሆኑን ያውቁ ኖሯል?"  በሚል ባጋራው መረጃ ኢትዮጵያ 2018 በጀት ዓመት  ከቡና ወጪ ንግድ 3.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስመዝግቧንም ጠቅሷል።

ይህም ሀገራችን ባለፉት 17 ዓመታት በአጠቃላይ ካገኘችው 3.3 ቢሊዮን ዶላር የገቢ መጠን ጋር የሚቀራረብ መሆኑን አብራርቷል።

ኢትዮጵያ የአረቢካ  ቡና መገኛ እና የአፍሪካ ቀዳሚ ቡና አምራች ሀገር መሆኗ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የቡና ፍሬ ተለቅሞና ተሰብስቦ ለዓለም የተበረከተው እዚሁ በኢትዮጵያ ምድር እንደሆነ ተመላክቷል።

ከእርሻ ማሳዎች እስከ ሲኒያችን ድረስ የአርሶ አደሩ እጅ ቤተሰብንና ማህበረሰብን የሚደግፍ ታላቅ ኃላፊነት እንደሚሸከም የጠቆመው መረጃው፤ ቡና እስኪፈላ በሚጠበቅበት ጊዜ ውስጥ ማህበራዊ ውይይቶች፣ ጥልቅ ትስስሮች እና የኢትዮጵያዊነት መግለጫ የሆነው የሰከነ ትዕግሥት በሙሉ እንደሚገለጥ ያብራራል።

በተጨማሪም በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በሚተከሉበት የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ውስጥ ሰፊውን ቁጥር የሚይዘው የቡና ችግኞች በመሆናቸው ደኖችን መልሶ የማቋቋም፣ ሥነ-ምህዳርን የመጠበቅ እና የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስፈልገውን አየር ንብረት መፍጠር ተችሏል።

 

ከዚህ ዕድገት ጎን ለጎን ኢትዮጵያ የቡና በሽታን ለመለየትና ለማከም የሚያስችሉ አዳዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂዎችን እና ምርምሮችን በማሳደግ ላይ መገኘቷ ምርትን ለማጠናከር እና የሰብሉን የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጠቀሜታ ይበልጥ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተገልጿል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: