በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ተምዝግቦ የዓለም ቅርስ የሆነው የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በብሔሩ ዘንድ እጅግ የተለየ ትኩረት የሚሰጥ የብሔሩ መገለጫ ነው።
ለበዓሉ ከዓመት እስከ ዓመት የእርድ በሬ መግዣና የእናቶች የቅቤ ቁጠባን የመሳሰሉ ዝግጅቶች የሚደረጉ ሲሆን፣ በዓሉ ሲቃረብ ግን ሳምንታት እና ቀናቶች የየራሳቸው ስያሜ አሏቸው።
በገበያዎች "ሀረ-ሀይቆ፣ ቦቦዳ እና ጎሻ" ቀናት "ኮሴታ ሐሙሳ፣ ሱልዓ አርባ፣ ባጭራ ቄራ እና ሹሃ ዎጋ" የሚባሉ የበዓሉ መዳረሻዎች ናቸው። የቀናቱ ስያሜ ከበዓሉ ማግስት "ታማ ሰኞ" ጀምሮ እስከ "ጎሏዋ እጌታ" ወደሚባልበት የበዓሉ ለቀጣይ ዓመት መልካም ምኞት ቀን ይቀጥላሉ።
በዚህ መሠረት ዛሬ በወላይታ ብሔር ዘንድ ቀኑ የዕርድ እሁድ" ሹሃ ዎጋ" በመባል ይጠራል። የዕርድ እሁድ አባቶች በ"Amuwaa" (በቡድን) አንድ ላይ ሆነው ከወራት በፊት ለእርድ የሚሆን በሬ ገዝተው ከቡድኑ አባላት በአንዱ ቤት የተቀለበው በሬ የሚታረድበት የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ነው።
የዕርድ በሬው በእሸት፣ በቆሎ፣ ስኳር ድንች እና በሌሎች እህልና ስራስሮች አባለቱ በየተራ እያዋጡ ይቀለባል። በሬ የሚታረደው "በአሙዋ" አባላት ውስጥ በሬ ሲቀለብ የቆየው አባወራ ደጅ ሲሆን፣ አባላት በዕርድ ቀን ጠዋት ተሰብስበው ከእርድ አስቀድመው በቦታው ባህላዊ ምግቦችን ይበላሉ፣ መጠጦችንም ይጠጣሉ።
በእርድ ቦታ ከስጋ ዓይነቶች የተወሰነ ወስደው የቡድኑ አባላት የአብሮነት መገለጫ ብለው በቦታው ይቋደሳሉ። የየራሳቸው ቅርጫ ከተከፋፈሉ በኋላ በእርጥብ ቆዳ ለሚቀጥለው ዓመት ጊፋታ በዓል የዕርድ በሬ መግዣ ተቀማጭ ገንዘብ ማስቀመጥ ይጀምራሉ።
ዕጣ ጥለው የተከፋፈሉትን ስጋ ወደየቤታቸው ከወሰዱ በኋላ እናቶች ቆጮ፣ ቂጣና ዳጣ በርበሬ በማዘጋጀት ሥጋውን የቤተሰቡ አባለት በጋራ በኮባ ቅጠል በመሬት ዘርግፈው ለማዕዱ ፈጣሪን በማመስገን በደስታ የበዓሉ ድግስ በጋራ ይበላሉ።
የዘንድሮ ጊፋታ በዩኔስኮ የተመዘገበበት የመጀመሪያ ዓመት በዓል በመሆኑ በወላይታ ሶዶ ከተማ በተለዬ ድምቀት “የትውልድ ቅርስን እንጠብቅ፣ የጊፋታን ውርስ እናስቀጥል” በሚል መሪ ቃል በአደባባይ እየተከበረ ይገኛል።
በትዕግስቱ ቡቼ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: