በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ ዞን የተገነቡት ሞዴል የገጠር መንደሮች ተመርቀው ለተጠቃሚዎች ርክብክብ መደረጋቸው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የነበረውን ባህላዊ የኑሮ ዘይቤ ወደ ዘመናዊነት የሚያሸጋግር ትልቅ ምዕራፍ ከፍቷል።
በዞኑ በጨና እና ሺሾንዴ ወረዳዎች በመንግስት፣ በተጠቃሚዎች እና በግል ባለሀብቶች የተቀናጀ ድጋፍ ተገንብተው የተመረቁት እነዚህ መንደሮች፣ ዜጎች በአካባቢያቸው ሆነው የተረጋጋና ዘመናዊ ሕይወት እንዲመሩ መደላድል ፈጥረዋል።
በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተበሰረው የሞዴል የገጠር መንደሮች ግንባታ የዜጎችን ሕይወት በተጨባጭ በመቀየር በገጠር ዘመናዊነት እንዲሰርጽ አድርጓል።
የመደመር መንግሥት የሕዝብን ሕይወት የሚያሻሽሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የክልሉ መንግስትም ለዚህ ስኬት የተቀናጀ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የመንደሮቹ መገንባት የገጠር ሽግግርን በማሳደግ በኅብረተሰቡ የኑሮ ዘይቤ ውስጥ ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩንና አሁን ላይ ይህ ልማት በ16 ወረዳዎች በተሟላ ሁኔታ መፈጸሙን አብራርተዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው የመንደሮቹ መገንባት ዜጎች በገዛ አካባቢያቸው ዘመናዊ የኑሮ ሁኔታን እንዲመሩ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በጣቢያው የተገኙ የሞዴል ገጠር መንደር ተጠቃሚዎችም ቀደም ሲል ረዥም ርቀት ተጉዘው ያገኙ የነበሩትን መሠረታዊ አገልግሎቶች አሁን በአቅራቢያቸው ማግኘት መቻላቸውን ገልጸው፣ ይህም ከዘመናዊነት ባሻገር ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ይበልጥ እንዳጠናከረው ተናግረዋል።
በሰለሞን ባረና
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: