ሁለተኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቴምር ፌስቲቫል ከአፋር ክልል መንግሥት፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከካሊፋ ዓለም አቀፍ የቴምር እና ግብርና ፈጠራ ድርጅት ጋር በመተባበር በአፋር ክልል መዲና ሰመራ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ይህ ሁነት የኢትዮጵያን የቴምር አምራችነት እምቅ አቅም ለዓለም ማስተዋወቅ፣ የቴክኖሎጂና የምርምር ውጤቶችን ልምድ ለሀገር ውስጥ አምራቾች ማጋራት ዋና ዋና ዓላማዎቹ አድርጎ የተነሳ ነው።
ከፍተኛ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር አምራቾች፣ ተመራማሪዎች፣ ባለሃብቶች እና የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
በመርሃ ግበሩ ላይ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በዘርፉ አዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመፍጠርና የገበያ ትስስርን በማጠናከር የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የውጭ ሀገር ቴምር ግዢን በመቀነስ ረገድ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የጠቆሙ ሲሆን፣ ይህ ፌስቲቫል የአፋር ክልልን እና የሌሎች ቆላማ አካባቢዎችን ተፈጥሯዊ ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም ትልቅ መንገድ የሚከፍት መሆኑ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ ከ500 ሺህ እስከ 700 ሺህ ሄክታር የሚደርስ ለቴምር ልማት ተስማሚ መሬት ያላት ቢሆንም እስካሁን ጥቅም ላይ የዋለው ከ1.2 በመቶ በታች መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።
ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ፌስቲቫል የተለዩትን ክፍተቶች በመድፈን ያልተነካውን አቅም ወደ ተጨባጭ ምርት ለመቀየር ሰፊ የምክክርና የትስስር ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በዕድሉ ፈቀደ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: