አረንጓዴ ዐሻራ የውኃ ሃብታችን እንዲጨምር አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ ቴክኒክ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ይግዛው አስታወቁ።
አቶ ጌታቸው ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከዚህም ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ገልጸዋል።
ላለፉት 7 ዓመታት በስፋት የተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አረንጓዴያማነት እንዲጨምር፣ ዘላቂ የሆነ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር እና የውኃ መጠን ከፍ እንዲል ማድረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የውኃ ኃይል አቅርቦት ላይ በስፋት እየሠራች በመሆኑ መርሐ-ግብሩ ለዚህ ሥራም ያግዛል ብለዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ጤናማ የሆነ አካባቢን እንደሚፈጥርም ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ የውኃ መነሻ ስፍራዎች ላይ አረንጓዴ የማልበስ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው እንዳሉት የአከባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴያማነት ከውኃ ጋር ያላቸው ትሥሥር የጎላ ነው።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው ትኩረት ያደረገው ግብርና ላይ በመሆኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በሚያመነጨው ውኃ ምክንያት ግብርናን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ውኃ ለግብርና፣ ለመዝናኛ እና ለኃይል አቅርቦት እንደሚያገለግል እና ለሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ አክለዋል።
በሜሮን ንብረት
#EBC #ebcdotstream #greenlegacy #waterresource