Search

ሉዓላዊነትን ከማስከበር እስከ ልማት አጋርነት የማይናወጠው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ አደራ

እሑድ ነሐሴ 03, 2018 116

የዓለም ሥልጣኔ ቀደምት የነበረችው ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ገናናነቷና ታላቅነቷ ተመልሳ ማየት የሠራዊቱ ልባዊ መሻት መሆኑን በማንገብ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን እናት ሀገሩን ከማንኛውም የጥፋት ቀስት በጽናትና በጀግንነት እየጠበቀ ይገኛል።

ሠራዊቱ ምንም ዓይነት ምድራዊ ፈተና ሳይበግረው የሀገራችንን ገጽታ ለመገንባትና ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ላይ ከሕዝብ ጋር እኩል እየተሳተፈ ነው።

የሞራልና የብርታት ምንጩ የሆነውን ሕዝብ በውል ያስቀደመው ይህ ሠራዊት፣ የሀገር ዕድገት ወሳኝ መሠረተ ልማቶች በጥፋት ኃይሎች እንዳይወድሙ እንደ ዓይኑ ብሌን ነቅቶ በመጠበቅ በየጊዜው በሚመዘገበው ሀገራዊ ለውጥ ላይ የበኩሉን ደማቅ አሻራ እያሳረፈ ይገኛል።

ለኢትዮጵያ ዕድገትና ለሕዝቡ ነፃነት መሰናክል የሚሆኑ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በጀግንነት ተፋልሞ በማክሸፍ የልማትን መንገድ እየጠረገ የሚገኘው መከላከያ ሠራዊቱ፣ የኢትዮጵያን ስምና ክብር አስጠብቆ ለመዝለቅ መክፈል የሚጠበቅበትን ውድ ዋጋ ሁሉ ያለ አንዳች ስስት እየከፈለ ነው።

እናት ሀገሩን ከአንድ ራሱና ነፍሱ አስበልጦ የሚመክተው ይህ ቆራጥ የሕዝብ ልጅ፣ ከምሥረታው አንስቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት በደሙ አንጽቶ ዳር ድንበሯን በአጥንቱ ፍላጻ እየማገረ ታሪክ ሠርቷል።

ከጅምሩ ሀገር ለመጠበቅ የተደራጀው ሕዝቡን መስሎ በመሆኑ፣ ይህ የተላበሰው ሕብረ ብሔራዊ ገጽታ እና ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ ጽኑ የሀገር ፍቅር ስሜት ጠላቶቹን ድል የሚነሳበት አስተማማኝ ትጥቁ ሆኗል።

በጥንት ዘመናት በሀገሩ የመጣበትን ጠላት በአይበገሬነት ድባቅ የመታው የኢትዮጵያ ወታደር፣ ዛሬ ላይ በወታደራዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ወደ ሥልጣኔ ማማ እየገሰገሰ ዘመኑን በሚገባ ዋጅቷል።

ከግዳጁ ጎን ለጎንም ለትውልድ ግንባታና ለሀገር አረንጓዴ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል በያዘችው ብሔራዊ ዕቅድ ከሕዝቡ ጋር በተቀናጀ መልኩ ያከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የዚሁ ቁርጠኝነት ማሳያ ነው።

ከዚህም አልፎ "የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ የማስገኘት" መርህን በመከተል በቀጠናው የሰላም ዋስትና መሆኑን ያስመሰከረው ሠራዊታችን፣ በአሁኑ ወቅት በደረሰበት የላቀ የዝግጁነት ደረጃ እና በታጠቀው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለየትኛውም ትንኮሳ ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት በተሟላ ቁመና ላይ ይገኛል።

በቴክኖሎጂ፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በጠንካራ አመራር የተገነባው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የማይናወጥ የሀገር ሉዓላዊነት ዓምድ እና እውነተኛ የሕዝብ አለኝታ መሆኑን በሁለንተናዊ ስኬቶቹ በተግባር አረጋግጧል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: