በተለያየ ማህበራዊ ችግር ውስጥ የነበሩ እና በለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በ5ኛ ዙር የክህሎት እና የስብዕና ግንባታ ስልጠናቸውን በተሳካ ሁኔታ ያጠናቀቁ 858 እህቶቻችን ዛሬ በደማቅ ሁኔታ ተመርቀው ወደ ስራ መሰማራታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
ከንቲባዋ በመልዕክታቸው ውድ ተመራቂ እህቶቻችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋቸዋል።
በከተማችን ከሚከናወኑ ሰው ተኮር ስራዎች መካከል ዋነኛው፣ ትላንት በጎዳና፣ በችግር እና በተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ውስጥ የነበሩ ሴቶችን በሙያ ክህሎትና ስብዕና ገንብቶ ከነበሩበት አስከፊ ህይወት በማውጣት ወደ ተሻለ ብሩህ ህይወት ማሸጋገር ነው ብለዋል ከንቲባዋ።
አዲስ አበባችን ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት እንዲሁም ለዘመናት የከረሙ ስብራቶቿ የሚጠገኑባት ከተማ እየሆነች ለመምጣቷ፣ ከለነገዋ ማዕከል ተመርቀው አዲስ ህይወት እየመሩ ያሉት እነዚህ እህቶቻችን ህያው የተግባር ፍሬ ማሳያዎች ናቸው።
የዛሬዎቹን ተመራቂዎች ጨምሮ ማዕከሉ እስካሁን በድምሩ 3 ሺህ 259 ሰልጣኞችን አስመርቆ ወደ ስራው ዓለም እንዲቀላቀሉ በማድረግ፣ ህይወታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲመሩና ለሌሎችም ትልቅ አርዓያ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል ከንቲባ አዳንች አቤቤ በመልእክታቸው።
ከንቲባዋ በመልእክታቸው ውድ ተመራቂዎች፤ አስከፊውን ትላንታችሁን አልፋችሁ በማዕከሉ ቆይታችሁ በቀሰማችሁት ክህሎት እና የተሀድሶ ስልጠና ዛሬን ማሸነፍ ችላችኋል። ነገም በስራው ዓለም ስኬታማ ለመሆን የሚገጥማችሁን ማንኛውንም ፈተና በዚሁ ጽናት አሸንፋችሁ ህይወታችሁን ይበልጥ ብሩህ እንደምታደርጉ ጽኑ እምነታችን ነው። በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: