Search

አሰብ ነዳጅ ማጣሪያ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ራዕይ እስከ ምድረ በዳነት የተጓዘበት አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ

እሑድ ነሐሴ 03, 2018 193

በ1960ዎቹ መጀመሪያ በንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድና አስጀማሪነት በአሰብ ከተማ የተገነባው የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ፣ ኢትዮጵያ በወቅቱ ያስፈልጋት የነበረውን የተጣራ የነዳጅ ፍላጎት በራሷ አቅም ለማሟላት የታለመ ግዙፍ የኢኮኖሚ እርምጃ ነበር።

የማጣሪያው ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ከበደ አካለወርቅ ያደረጉትን ንግግር ጠቅሶ የተዘጋጀ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ፕሮጀክቱ በወቅቱ 55 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን፣ ሙሉ ወጪው ከሶቪየት ኅብረት በተገኘ የብድርና የቴክኒክ ድጋፍ በሩሲያውያንና በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ቅንጅት የተገነባ ነበር።

እንደ ኢንጂነር ከበደ ማብራሪያ፣ በወቅቱ እንደ ሌሎች ሀገራት የተጣሩ የነዳጅ ምርቶችን ከውጭ ከመግዛት ይልቅ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደር ማጣሪያ መገንባቱ ለኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦት ነፃነት ትልቅ ማረጋገጫ ነበረ።

ይህ ግዙፍ ማጣሪያ በመጀመሪያው ምዕራፍ በዓመት 500 ሺህ ሜትሪክ ቶን ነዳጅ የማጣራት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ሲሆን፣ በ1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታ 300 ሺህ ሜትሪክ ቶን ገደማ ስለነበር፣ የማጣሪያው አቅም ከፍላጎት በላይ በመሆኑ ለተከታታይ ዓመታት ያለምንም ስጋት አቅርቦቱን ማሟላት ችሎ ነበር።

ከ1966ቱ አብዮት በኋላ የመጣው የደርግ ወታደራዊ መንግሥትም የማጣሪያውን የማምረት አቅም ከ500 ሺህ ወደ 800 ሺህ ሜትሪክ ቶን አሳድጎት እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል።

በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም የደርግ መንግሥት ሲወድቅና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገንጠልም፣ ማጣሪያው እስከ ግንቦት 1989 ዓ.ም ድረስ ለኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠቱን ቀጥሎ ነበር።

ሆኖም በኋላ በተነሳው ጦርነት ምክንያት አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ሊቋረጥ ችሏል። ኢትዮጵያን ከባህር በር እስከ ነዳጅ ማጣሪያ፣ እንዲሁም ከንግድ መርከቦች እስከ ባህር ኃይል በሴራ ለባዕድ ሀገር አሳልፎ የሰጠው ህገ ወጡ የህወኃት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

ያለምንም መንግስታዊም ሆነ ህዝባዊ ስምምነት ይህንን ትልቅ የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት ለባዕድ ሀገር አሳልፎ የሰጠው ህገ ወጡ ቡድን፣ ኢትዮጵያን በመክዳት የእናት ጡት ነካሽነቱን በተጨባጭ አረጋግጧል።

በዚህ የክህደት ሴራ የተነሳ ሀገራችን የራሷን ሃብት እንድታጣ ከመደረጉም በላይ፣ ግዙፉ የአሰብ ነዳጅ ማጣሪያ ባለፉት 29 ዓመታት ያለምንም ጥገናና ጥበቃ ቆሞ የብረት ክምርና ምድረ በዳ ሆኖ ቀርቷል።

በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: