Search

ከግጭት ውጭ ህልውና የሌለውና በ1960ዎቹ እሳቤ ተቸንክሮ የቀረው ኋላቀሩ የሕወሓት ቡድን ማንነት

እሑድ ነሐሴ 03, 2018 133

የስምረት ፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ሀብቱ ኪሮስ በቅርቡ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳጋለጡት፣ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በ1960ዎቹ የነበረውን ያረጀ እሳቤና የፖለቲካ የጦርነት ዘፈን እያዜማ የሚኖር፣ ከዘመኑ ጋር መራመድ የማይችልና አዲስ ሀሳብን ፈጽሞ የማይቀበል ቆሞ-ቀር ስብስብ ነው።

ይህ የጥፋት ኃይል ከቀደመ ማንነቱ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በትርምስና በግጭት ጎዳና ላይ ብቻ የሚጓዝ፣ ከግጭትና ከደም መፋሰስ ውጭ መኖር የማይችል እኩይ ቡድን መሆኑን አመራሩ በግልጽ አስረድተዋል።

ሕወሓት በባህሪው የነፍጥ እና የኃይል መንገድን ብቻ የሚያምን፣ የሀሳብ ሙግትን የማይቀበልና በድንቁርና ጉዞ ውስጥ ሆኖ ጠብመንጃ በማንሳት ብቻ ፍላጎቱን በሌሎች ላይ ለመጫን የሚፈልግ ጠብ አጫሪ ቡድን ነው።

ይህ የጥፋት ባህሪው ቡድኑን ከአንድ የውድመት ምዕራፍ ወደ ሌላ የትርምስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አድርጎታል ብለዋል።

በ1960ዎቹ የህዝብን ስሜት ለማቀጣጠል ይጠቀምባቸው የነበሩትን ያረጁ መፈክሮችና ዘፈኖች ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሊጭን ይሞክራል።

ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ "እምበር ተጋዳላይ" የሚለው ያረጀ ትርክት በፍጹም የማይሰራና የትግራይ ወጣትም ከቶውንም የማይቀበለው ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት የትግራይ ወጣቶችና አርቲስቶች የቡድኑን ኋላቀር ማንነትና ያረጁ መዝሙሮች በጥበብና በሠለጠኑ ሀሳቦች እየተኳቸው ይገኛሉ።

አርቲስቶቹ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው የጦርነት ጋጋታን የሚደግፍ ዘፈን እንዲዘፍኑ ከቡድኑ ከፍተኛ ተጽዕኖ ቢደረግባቸውም፣ ፍላጎታቸውና ተነሳሽነታቸው የህዝብን ሰላም መጠበቅ በመሆኑ ይህን ህገ-ወጥ ጥሪ ሊቀበሉት አልቻሉም።

አሁን የትግራይ ህዝብ የሚያስፈልገው የፍቅርና የልማት ዘፈን ነው ያሉት አመራሩ፣ ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያዎች የዚህን ኋላቀር ቡድን እኩይ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያደርገውን ትግል አድንቀው፣ የዚህ ዘመን ባለቤት ወጣቱ በመሆኑ የራሱን የሰላም መንገድ መከተል እንዳለበት አሳስበዋል።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የፌደራል መንግስት የሀገርን ድንበር የመጠበቅ ህገ-መንግስታዊ ሀላፊነት እንዳለበት የጠቆሙት አቶ ሀብቱ፣ ህገ ወጡ ሕወሓት "የፌደራል መንግስት ከቦኛል" እያለ የሚያቀርበው ሰበብ  የግጭት አባዜውን ለማርካት የሚጠቀምበት አላስፈላጊ ቀልድ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ቡድን እራሱን እንደ ኢትዮጵያዊ አድርጎ ማሰብ ካቆመ ውሎ አድሯል። በሀሳብ የተሸነፈና ያለችውን ህገ-ወጥ ቁመና በጠመንጃ ብቻ ለማቆየት የሚጣጣር ቆሞ-ቀር ቡድን ቢሆንም፣ የትግራይ ህዝብ ግን ለሀገሩ ብዙ ዋጋ የከፈለና በማንኛውም መለኪያ ኢትዮጵያዊ መሆኑን አብራርተዋል።

ሕወሓት ኢትዮጵያዊነትን እንደ አማራጭ የፖለቲካ ካርድ ብቻ እንደሚጠቀምበትና የራሱን ኋላቀር ሀሳብ በትግራይ ህዝብ ላይ በኃይል ለመጫን እንደሚሞክር ያጋለጡት አቶ ሀብቱ ኪሮስ፣ የትግራይ ህዝብ ሰላም፣ ፍቅርና ልማት የሚሻበት ጊዜ ላይ በመድረሱ ይህ የቡድኑ ያረጀ የጦርነት ዘፈን ከእንግዲህ አዳማጭ እንደሌለው አረጋግጠዋል።

በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: