"የፖለቲካ ነፃነት ወደ ውይይት፣ ውይይት ደግሞ ወደ የሕግ የበላይነት ያድጋል" ይህ ሐሳብ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ንግግር የተወሰደና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ተፈጥሯዊ ሂደት በጥበብ የሚያሳይ ፅንሰ-ሐሳብ ነው።
አንድ ሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የሚችለው እነዚህን ተከታታይ ደረጃዎች በትክክል ተረድቶ ተግባራዊ ሲያደርግ ብቻ በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የዚሁ እውነት ተግባራዊ ማረጋገጫና ለሀገራችን ብሩህ ተስፋ ማብሰሪያ ሆኗል።
የፖለቲካ ነፃነት የመጨረሻው ግብ ሳይሆን የመንገዱ መጀመሪያ ነው። ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ዜጎችና የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ያለምንም ስጋት በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጡ መንገድ ይከፍታል።
የፖለቲካ ምህዳሩ ክፍት መሆን ደግሞ ሀገራዊ ልዩነቶችን በኃይል ከመፍታት ይልቅ በሰለጠነ የንግግር ባህል ለመፍታት ያስችላል። ስለሆነም የፖለቲካ ነፃነት መስፈኑ ወደ ተሻለና ወደተደራጀ ሀገራዊ ውይይት የሚወስደን የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ ነው።
በውይይት ያልተደገፈ የፖለቲካ ነፃነት ወደ ያልተገደበ ብጥብጥና ሥርዓት አልበኝነት ሊያመራ ስለሚችል፣ ነፃነቱን ወደ አዎንታዊ ሀገራዊ ኃይል የሚቀይረው እውነተኛና አካታች ውይይት ነው።
ውይይት በግለሰቦችና በቡድኖች መካከል ያሉ የመስማማት እና የመለያየት ነጥቦችን በግልጽ በማውጣት ለሕጎች፣ ለፖሊሲዎችና ለህገ-መንግሥታዊ ማሻሻያዎች መሠረት ይሆናል።
የሕግ የበላይነት የሚረጋግጠው ሕጎች የሁሉም ዜጎች የጋራ ስምምነት ውጤት ሲሆኑ በመሆኑ፣ አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ይህንን የሚተረጉም ታሪካዊ መድረክ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ውዝግቦችን በዘላቂነት ለመፍታት ከቀድሞው የኃይልና የእርስ በእርስ ግጭት አካሄድ ተላቃ ወደ ሀገራዊ የምክክር ምዕራፍ ተሸጋግራለች።
በታሪካዊ እና ፖለቲካዊ አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ የጋራ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር፣ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት፣ እንዲሁም ፍትሐዊና የሕግ የበላይነት የነገሠባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት መሠረት መጣል ከጉባኤው ዋና ዋና ግቦች ተጠቃሽ ናቸው።
የፖለቲካ ነፃነት ምቹ ሁኔታን ሲፈጥር፣ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ደግሞ ያንን ነፃነት ወደ ፍሬያማ ውይይት የመቀየር ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል።
ከጉባኤው የሚወጡት ውጤቶች ጠንካራ ተቋማትንና የሕግ የበላይነትን ለምትገነባዋ ቀጣይዋ ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥሉ በመሆናቸው፣ ይህ የምክክር ሂደት የሁሉም ዜጎች፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሣትፎና ድጋፍ የሚያስፈልገው ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: