Search

ጠንካራ ዝግጅት ለዘላቂ ሰላም፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አስተማማኝ ቁመና

ሰኞ ነሐሴ 04, 2018 177

በዓለም አቀፍ የደኅንነት ሳይንስ ውስጥ ሰላምን የሚሻ ሀገር ለጦርነት መዘጋጀት እንዳለበት ይነገራል። ይህ የዘመናት ጥበብ በኢትዮጵያ የመከላከያ ስትራቴጂ ውስጥ "በቂ ዝግጅት ጦርነትን ያስቀራል" በሚል መሪ መርህ ተቀርጾ በከፍተኛ ትኩረት እየተተገበረ ይገኛል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በተለያዩ መድረኮች እንዳብራሩት፣ ኢትዮጵያ ሠራዊቷን በሁለንተናዊ መልኩ እያዘጋጀች ያለችው የጦርነት ፍላጎት ኖሯት ሳይሆን ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን አስቀድሞ ለማክሸፍ እና የሀገርን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግርም "በቂ ዝግጅት ስላለን ማንም አያስቆመንም፤ ዝግጅት የምናደርገውም ጦርነትን ለማስቆም ነው" በማለት የመከላከያ ተቋሙን የገቺነት አቅም ፍልስፍና በግልጽ አስቀምጠዋል።

በታሪካዊ ዳራ ሲታይ ኢትዮጵያ የሌሎችን ሉዓላዊነት በማክበር ላይ የተመሠረተ የውጭ እና የመከላከያ ፖሊሲ ያላት ሀገር ናት። በረጅም ታሪኳ የማንንም ሀገር ድንበር ገፍታም ሆነ የሌላውን የተፈጥሮ ሀብት ፈልጋ በወረራ መልክ መሬት ይዛ አታውቅም።

በተቃራኒው ሌሎች ኃይሎች ድንበሯን ሊገፉ ሲሞክሩ በምታደርገው ጥብቅ ዝግጅት የታሪካዊ ጠላቶቿን ጥቃት በብቃት ስትመክት ኖራለች። የውጭ ወራሪ ኃይሎች ሉዓላዊነቷን ለመጣስ በሞከሩበት ወቅት ለመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራት የሆነው ሠራዊት ወረራውን በመመከት የሀገርን ዳር ድንበር ያስከበረበት የዓድዋ ድል ለዚህ ታሪካዊ እውነት ዋነኛ ምስክር ነው።

ይህ እውነታ እንደሚያሳየው ሀገራችን ሁልጊዜም ዝግጅቷን የምታጠናክረው የራሷን ህልውና ለመጠበቅ እንጂ በወራሪነት ለመሰማራት አይደለም።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አሁን ላይ በሰው ኃይል ብዛት ላይ ብቻ ሳይሆን በጥራት፣ በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ እና በላቁ ቴክኖሎጂዎች ላይ የተመሠረተ አስተማማኝ አቅም ገንብቷል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ አቅሙን ቢያንስ በሁለት እጥፍ ለማሳደግ ግልጽ ዕቅድ ይዞ እየሠራ ሲሆን፣ ከአራተኛ ትውልድ የውጊያ አውሮፕላኖች ወደ አምስተኛ ትውልድ የማሸጋገር ሂደት ላይ ይገኛል።

በዚህም የሱ-30 እና -10 የጦር አውሮፕላኖች አቅም፣ የላቁ ሰው-አልባ አውሮፕላኖች እና የኤሌክትሮኒክስ ውጊያ መሣሪያዎች ተቀናጅተው ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። በተጨማሪም የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ዘመናዊ የስለላ ድሮኖች እና በትክክል ዒላማ ይመቱ ዘንድ የተደራጁ ልዩ የኮማንዶ ኃይሎችን በማሰማራት የሀገራችንን ስትራቴጂካዊ ሀብቶች በንቃት እየጠበቀ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ወታደራዊ ስትራቴጂ ከየብስ ውጊያ ባለፈ የባሕር ኃይል አቅምን እና የውኃ ሀብቶችን ደኅንነት የመጠበቅ ብቃትን በማካተት፣ ሀገራችን በቀጣናው ባሏት ወንዞች እና ግድቦች ላይ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር አቅም ፈጥሯል።

ይህ የሠራዊቷ ብቁ ዝግጅት እና የገቺነት አቅም ብሔራዊ ጥቅሟን ለሚፈታተኑ ታሪካዊ ጠላቶቿ ጠንካራ መልእክት የሚያስተላልፍ እና ሀገራችን ክብሯን በየዋህነት አሳልፋ እንደማትሰጥ የሚያረጋግጥ ነው።

ሠራዊቱ የሀገራችንን አየር፣ የብስ እና የሳይበር ምኅዳር በየሰከንዱ በንቃት በመጠበቁ ምክንያት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች የታሪካዊ ጠላቶችን የጥፋት ሙከራ ተሻግረው ሊጠናቀቁ ችለዋል።

በቀጣናው የሚገኙ ታሪካዊ ጠላቶች የሕዳሴ ግድብን ግንባታ ለማስተጓጎል ያደረጓቸውን ሊነገሩ የማይችሉ የሳቦታጅ ሙከራዎችን በማክሸፍ ረገድ የመከላከያ እና የደኅንነት ተቋማት የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።

ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካት የምትችለው ይህ ጠንካራ የመከላከያ ተቋም ሲኖር ብቻ መሆኑ በግልጽ ታይቷል።

በሀገራዊ ለውጡ መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገናዊነት ነፃ ሆኖ የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ የሕዝቦቿን ደኅንነት እና ብሔራዊ ጥቅሟን ብቻ የሚጠብቅ ሕዝባዊ ተቋም ሆኖ እየተገነባ ይገኛል።

በአዋጅ ቁጥር 1286/2015 በተደረገው ማሻሻያም ተቋሙ የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሚዛናዊ ተዋፅኦ ያካተተ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ሆኖ ተገንብቷል። ሠራዊቱ በውጊያ ጊዜ አደጋ ሲደቀን ከራሱ በፊት ለሕዝቡ እና ለሀገሩ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ጽኑ ኃይል መሆኑን በተደጋጋሚ በተግባር አስመስክሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃም በሩዋንዳ፣ በሱዳን እና በሶማሊያ ባከናወናቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የታመነ፣ ጀግና እና ዲሲፕሊን ያለው ኃይል መሆኑን በማረጋገጥ ትልቅ ስምና ዝና አትርፏል።

በሰላም ጊዜ ደግሞ ሠራዊቱ የልማት እና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማዕከል በመሆን ሀገርን ወደ ላቀ ከፍታ እያሻገረ ይገኛል። እንደ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተቋማቱ ወደ ዘመናዊ የምርምር፣ የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከላትነት ተሸጋግረው ለሀገር የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

ሠራዊቱም ከወታደራዊ ግዳጁ ጎን ለጎን በግብርና፣ በመሠረተ-ልማት እና በተለያዩ ሀገራዊ የልማት ሥራዎች ላይ በቀጥታ በመሳተፍ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማፋጠን ላይ ይገኛል።

ይህ ሁለንተናዊ ዝግጅት፣ ቴክኖሎጂያዊ ሽግግር እና ተቋማዊ የሪፎርም ስራ የኢትዮጵያን ዘላቂ ህልውና የሚያረጋገጥ እና ጦርነትን በማስቀረት ሰላምን የሚያፀና ጽኑ ብሔራዊ ምሰሶ መሆኑን መላው ሕዝባችን በጽኑ ሊገነዘበውና በሠራዊቱ ላይ ያለውን የማይናወጥ እምነት ሊያጎለብት ይገባል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: