በደቡባዊ ኖርዌይ የምትገኘው የርጁካን ከተማ የፀሐይ ብርሀን የምታገኘው በተራሮች ላይ በተተከሉት ትላልቅ መስታወቶች አማካኝነት ነው፤ መስታውቶቹ ከፀሐይ የሚያገኙትን ብርሃን በማንፀባረቅም ለከተማዋ ያደርሳሉ።
ከተመሰረተች ከመቶ ዓመት በላይ የሆናት የርጁካን ከተማ ቬስተፊዎርድ በመባል በሚታወቀው ሸለቆ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ በየዓመቱ ከመስከረም እስከ መጋቢት ድረስ ባሉት ወራት በቀጥታ የፀሐይ ብርሀን እና ሙቀት አይደርሳትም።
ለዚህ የዳረጋት ደግሞ በትላልቅ ተራሮች በመከበቧ ነው።
ጋስታቶፐን 1 ሺ 800 ሜትር ቁመት ያለው እና የቬስፊወርድ ሸለቆን ከበው ከሚገኙ ተራሮች መካከል አንደኛው ነው።
በክረምት ወራትም ወደ ከተማዋ የሚደርሰው የፀሐይ ብርሀን በዚህ ተራራ ስለሚሸፈን የራጁካን ከተማ ከፀሀይ ብርሀን ተከልላ በግዙፉ ተራራ ጥላ ትጋረዳለች ።
ለዘመናት በዚህ መልኩ ለመኖር የተገደዱት የርጁካን ከተማ ነዋሪዎች በአንድ ወቅት በክረምት የፀሐይን ሙቀት እና ያልተከለለ ብርሀን ለማግኘት በኬብል በተሰራ መጓጓዣ እየተጠቀሙ ተራሮች ወደማይከልሉት አካባቢ ይጓዙ ነበር ።
የርጁካን ከተማ የመቶ ዓመት ህልም
ሳም አይዲ ይባላል ከመቶ ዓመታት በፊት በ1913 የራጁካን ከተማን የመሰረተ ሰው ነው።
ይህ ሰው በወቅቱ እሱም ሆኑ ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች የፀሐይን ብርሀን ለማግኘት መስታወት መጠቀምን እንደ መፍትሄ ሃሳብ አምጥቶ ነበር ።
ሆኖም በወቅቱ ያለው የቴክኖሎጂ እድገት ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ባለመሆኑ የሳም አይዲ ሀሳብ ከወረቀት ያላለፈ ሆኖ መቶ ዓመታትን አሳልፏል ።
ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ግን ማርቲን አንደርሰን የሚባል በከተማዋ የሚኖር አንድ ሰዓሊ ይህንን ሀሳብ ወደ እውን ለመለወጥ መንቀሳቀስ ጀመረ። እ.አ.አ. በ2013 ላይ ይህን የከተማዋን ችግር ያየው የስነ-ጥበብ ባለሙያ አንድ መፍትሄ አመጣ።
ይህ የርጁካን ከተማን የተወሰነ ክፍል የፀሐይ ብርሀን እንዲያገኝ ያስችላል ተብሎ የታሰበውን አዲስ ሃሳብም ከተራራው አናት ላይ ትላልቅ መስታወቶችን መትከል የሚል ነበር ።
ይህን ሥራ በእውቀታቸው የሚያግዙት መሀንዲሶችንና ለግንባታው የሚያስፈልገውን አምስት ሚሊየን ክሮነር ካሰባሰበ በኋላ ሥራው ተጀምሮ ከጥቂት ዓመታት በፊት ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ ።
በዚህም መሰረት የእያንዳንዳቸው ርዝመት 17 ሜትር ካሬ ስኩየር የሚሆኑ ሶስት ግዙፍ መስታወቶች በጋስታቶፕን ተራራ ላይ ተተክለው የፀሐይ ብርሀንን ወደከተማዋ እንዲያንፀባርቁ ተደረገ።
እነዚህ በኮምፒውተር የሚታገዙት ከከተማዋ 450 ሜትር ከፍታ ላይ የተተከሉት "ሄሎስታት" በመባል የሚጠሩ መስታወቶች የፀሐይን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ እንደ ሱፍ አበባ መዟዟር እንዲችሉ ተደርገው የተሰሩ ናቸው። ለዚህ የሚያገለግላቸውን የኤሌትሪክ ኃይልም ከፀሐይ እና ከንፋስ ያገኛሉ።
በዚህ መሰረት በመስታወቱ ላይ የሚንፀባረቀው የፀሐይ ብርሀን ወደከተማዋ ይደርሳል። 600 ሜትር ስኩየር ለሚሆነው የከተማዋ ዋና አደባባይ እና በገበያ ቦታዎች ላይም ከፀሐይ ብርሀን የተቀበሉትን ብርሀን እና ሙቀት ከ80 እስክ 100 በመቶ በማድረስ ውጤታማ ሆነዋል።
ታዲያ እነዚህን መስታወቶች መጠጋት ለከፍተኛ የጤና እክል እንደሚዳርግ ባለሙያዎች ያሳስባሉ። በሩቁ የሚያደርሱት ብርሃን ግን ለብዙዎች መላ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ከተመሰረተች ጀምሮ በዓመት ግማሹን ጊዜዋን በተራራ ተጋርዳ ታሳልፍ የነበረችው የርጁካን ከተማ ነዋሪዎች አሁን ላይ በተተከሉት መስታወቶች አማካኝነት በሚደርሳቸው የፀሐይ ብርሀን እና ሙቀት ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ሌላ ከተማዋ የቱሪስት መስህብ ለመሆን ችላለች።