ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ኢትዮጵያን ከወጣቶቿ ነጥሎ ማየት አይቻልም" በማለት፣ ወጣቶች ለሀገር ብልጽግና፣ ሉዓላዊነት እና ሁለንተናዊ ለውጥ ያላቸውን ወሳኝ ሚና የሚያጎላ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ የዕድሜ ስብጥር ወጣቱ ከፍተኛውን ቁጥር መያዙን እንደሚያመላክት ጠቅሰው፣ ይህ ደግሞ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ እና ለማጽናት ታላቅ ዕድል መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ወጣት መልካም ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀስ የለውጥ ዋነኛ ሞተር እና የሉዓላዊነት ጽኑ ማገር መሆኑንም አክለዋል።
የአሁኑ ዘመን ወጣት ሀገራችንን ወደ ኋላ ከሚጎትቱ አጓጉል ልማዶች፣ አላስፈላጊ ንትርኮች፣ ጭቅጭቆች እና ግጭቶች ራሱን በማራቅ በልማት ላይ ብቻ ማተኮሩን እና ድህነትን መጸየፉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።
በዚህም ተግባሩ ወጣቱ የሀገሩን ታሪክ በአዲስ ብዕር እና ብራና እየጻፈ እንደሚገኝ መስክረዋል።
የመደመር መንግሥት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና የአመራርነት ሚና ለማጠናከር በልዩ ትኩረት እና በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።
ሀገራዊ ራዕይን ዕውን ለማድረግ ሁሉም ዜጋ በንቃት እየተጋ እና በፍቅር እንዲመላለስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: