Search

“የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለአፍሪካ ሀገራትም ጭምር መልካም ተሞክሮ የሚሆን ታሪካዊ መድረክ ነው” - ተመካካሪዎች

ረቡዕ ነሐሴ 06, 2018 37

እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር አርአያ የሚሆን መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።

በመድረኩ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ 4 ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

ተመካካሪዎቹ እንዳሉት፤ በውይይቱ እየተነሱ ያሉት ሐሳቦች ሀገራዊ ሰላምን፣ ዴሞክራሲን እና አብሮነትን ለማጠናከር ጠንካራ መሠረት የሚጥሉ ናቸው።

ከተመካካሪዎች መካከል ወጣት ዳንኤል ሲሳይ፣ የሀገራዊ ምክክር የእስካሁን ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ እና ትልቅ ሀገራዊ ተስፋ የሚታይበት መሆኑን ተናግሯል።

ሂደቱ የትውልድ ዕጣ ፈንታን በባለቤትነት በመቅረጽ ረገድ ታሪካዊ ፋይዳ እንዳለው በመገንዘብ የሚካሄድ በመሆኑ፤ በተለይም ለመጪው ትውልድ፣ ታዳጊዎች እና ለወጣቶች ብሩህ ተስፋን የፈነጠቀ መሆኑንም አብራርቷል።

አቶ ጸድቻ ሌሌ በበኩላቸው መድረኩ አካታች፣ መከባበር የተሞላበት፣ ሁሉም ሰው በነፃነት ሀሳቡን የሚያንሸራሽርበት እና ጠንካራ ህብረት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

እያንዳንዱ ተመካካሪ ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚቻል በማመንም፣ ስሜቱንና ሀሳቡን በግልጽ ያንጸባረቀበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ፋራህ ወርሰመ በበኩላቸው፣ እየተካሄደ ያለው የምክክር ሂደት ሁሉንም ያሳተፈ እና የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ሰፊ ዕድል የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በውይይት ለመፍታት በአንድነት የተሰበሰቡበት ታሪካዊ አጋጣሚ በመሆኑ ከጉባኤው የሚጠበቀው ውጤት አዎንታዊ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

አክለውም ይህ አሳታፊ ሂደት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደ መልካም ተሞክሮ እና ሞዴል ሊወስዱት የሚችሉበት መሆኑን በመጠቆም፤ በጉባኤው የተገኙት ገንቢ ውይይቶች እና የተደረሱ ስምምነቶች ለቀጣይ ሰላም፣ ዕድገት እና አብሮነት ታላቅ ምዕራፍ የሚከፍቱ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: