Search

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ፡ የሰላም፣ የዕድገት እና የቀጣናዊ ትስስር መንገድ

ረቡዕ ነሐሴ 06, 2018 67

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከጂኦፖለቲካዊ ፍላጎት ባሻገር፣ 130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ካላት ሀገር የህልውና እና የኢኮኖሚ እድገት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ታሪካዊ እንዲሁም ስትራቴጂያዊ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያን በቀይ ባሕር ቀጣና ያላት ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ትስስር በቀላሉ የሚዘነጋ አይደለም።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ቀይ ባሕርን እና የቀይ ባሕርን የንግድ መስመር ስትጠቀም የቆየች፣ ከአክሱም ሥርወ መንግሥት ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜው ዘመናዊ የባሕር ኃይል ምስረታ ድረስ ጠንካራ የባሕር ላይ ተጽዕኖ የነበራት ጥንታዊት ሀገር ነች።

ነገር ግን 20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በነበሩ ፖለቲካዊ ሁነቶች ምክንያት የባሕር በር አልባ ለመሆን ተገዳለች።

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታትም 90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የገቢ እና የወጪ ንግዷን በአንድ ጎረቤት ሀገር ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ እንድትሆን ተገድዳለች።

ይህ ሁኔታ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና አምጥቷል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ እና ተያያዥ የሎጂስቲክስ ወጪዎች በየዓመቱ 1.5 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች።

ይህ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች፣ ለመሰረተ ልማት እና ለዜጎች ማኅበራዊ አገልግሎት ሊውል የሚችል ግዙፍ ሀብት ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ያለ በፍጥነት የሚያድግ ኢኮኖሚ እና ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ያለው ሀገር በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ተደራሽነቱን መወሰኑ በምንም መለኪያ ዘላቂነት የለውም።

በመሆኑም የባሕር በር አማራጮችን ማስፋት እና የራስዋ የሆነ ዘላቂ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ማቅረቧ ለወደፊት ኢኮኖሚያዊ ዘላቂነት እና ለዓለም አቀፍ የንግድ ውድድር ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ይታመናል።

ይህ የባሕር በር ጥያቄ በኃይል ወይም በግጭት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ፣ በጋራ ልማት እና ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ በሚሆኑበት የመስጠት እና የመቀበል ዲፕሎማሲያዊ መርሕ ላይ የተመሰረተ ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነትን ስታገኝ፣ ለጎረቤት ሀገራት የኢነርጂ፣ የንጹህ ውኃ እና የገበያ ዕድሎችን በማቅረብ የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር ትችላለች።

ከዚህም ባለፈ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም ባሉ ግዙፍ ተቋሞቿ ላይ ድርሻ በማካፈል፣ መተማመን ላይ የተመሰረተ ትብብር ለመፍጠር ዝግጁ መሆኗን በተግባር እያሳየች ነው።

ይህ አዎንታዊ አካሄድ ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እና የጋራ ብልጽግና ጠንካራ መሰረት የሚጥል ታሪካዊ ሂደት ነው።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: