የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሁን ላይ የደረሰበት ምዕራፍ የሀገራችንን ዘለቄታዊ ሰላም እና መረጋጋት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጉዞ ምን ያህል ጥልቅ እና ለረጅም ጊዜ የቆየ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
አንድ ወር ገደማ የተከናወኑት ሥራዎች እና የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የሰጡት ማብራሪያ እንደሚያመለክተው፣ ሂደቱ ወደ ወሳኙ የሐሳብ መሰባሰብ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል።
ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ሂደት በተገቢው ጥልቀት እና ሳይንሳዊ የውይይት ሥነ ሥርዓት መነጽር መመልከት ለውጤታማነቱ ወሳኝ ነው።
ሀገራዊ ምክክር በባህሪው ቀላል እና በአንድ ጀምበር የሚጠናቀቅ የቀጥታ መስመር ሂደት አይደለም። በብዙ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ስብራቶች ውስጥ ያለፈች ሀገር ተወካዮች በአንድ አዳራሽ ሲሰበሰቡ አለመግባባቶች፣ ጭቅጭቆች እና የስሜት መጋገሎች መከሰታቸው የሂደቱ ተፈጥሯዊ አካል ነው።
የማኅበራዊ ሳይንስ እና የምክክር ሂደቶች የሚያስተምሩን ግን፣ የውይይት የመጀመሪያው ምዕራፍ “የተበታተነ ሐሳብ እና የስሜት መግለጫ ምዕራፍ” በመሆኑ፣ እያንዳንዱ አካል ለዘመናት አምቆ የያዘውን ቁጭት፣ ቅሬታ እና ጥያቄ ይዞ ብቅ ማለቱ አወንታዊ መሆኑን ነው።
ጭቅጭቅ እና ክርክር የውይይቱ ማክተሚያ ሳይሆኑ፣ ወደ መሐል ለመምጣት እና የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ የሚያስችሉ የመጀመሪያ እርምጃዎች ናቸው።
ይህ ሂደት የ4 ሺህ ተመካካሪዎችን ድምፅ የሚያስተናግድ ነው። እነዚህ ተሳታፊዎች ከሚኒስትሮች እስከ አርሶ አደር እና አርብቶ አደር ያሉ፣ የ130 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ስሜት እና ጥያቄ ከጀርባቸው ተሸክመው የመጡ ናቸው።
ስለዚህም የሐሳቦች መጋጨት እና የመቃወም ድምፆች መሰማታቸው የሂደቱ ሕያውነት ማረጋገጫ እንጂ ያለመሳካት ምልክት ሊሆን አይችልም።
በምክክሩ ሂደት ውስጥ ከተስተዋሉት ዋና ዋና ተፎካካሪ ፍላጎቶች አንዱ ተመካካሪዎች የመጡበትን አካባቢ አጀንዳ ብቻ ወደፊት የመግፋት ፍላጎት ነው። ይህ ለዘመናት ሲጠየቁ ለነበሩ ጥያቄዎች መፍትሔ ለመፈለግ ካለ እውነተኛ ስሜት የሚመነጭ ቢሆንም፣ የምክክሩ ዋና ማዕከል ግን ኢትዮጵያ ናት።
ተመካካሪዎች ከአካባቢያዊ እና ቡድናዊ ፍላጎት ወጥተው ወደ መሐል በመምጣት የጋራ ሀገር ግንባታ ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ የሂደቱ ዋና ግብ ነው።
ይህም ማለት የአካባቢ ጥያቄዎች አይደመጡም ማለት ሳይሆን፣ ጥያቄዎቹ ሁሉ የሚመለሱባት እና የሚስተናገዱባት ሀገራዊ ማዕቀፍ ላይ መስማማት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ነው።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የመላው ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎችን በእኩል ደረጃ ለማዳመጥ እና ለመፍታት የቆመ ገለልተኛ ተቋም ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ፡
የመደማመጥ እና የመከባበር መርሕ፦ በውይይቶች ወቅት የሥነ-ምግባር ግድፈቶች (ሰውን ማሻማቀቅ ወይም ማንጓጠጥ) በምክክሩ ደንብ መሠረት ፍጹም የተከለከሉ ናቸው።
የትዕግሥት እና የጥበብ አመራር፦ ኮሚሽኑ ተሳታፊዎቹን እንደ ትምህርት ቤት ተማሪዎች “አጥፍተሃል፤ ና ውጣ” በሚል የማግለል እርምጃ ከመቅጣት ይልቅ፣ የሁሉንም ትልቅነት እና የጀርባቸውን ሕዝባዊ ውክልና በማከበር ነገሮችን በትዕግሥት እና በውይይት የመፍታት አካሄድን ተከተሏል።
የአቤቱታ ማስተናገጃ ሥርዓት፦ በቃላት አጠቃቀም ወይም በሐሳብ አለመካተት ላይ የሚነሡ ቅሬታዎችን የሚቀበሉ ከፍተኛ ኤክስፐርቶች እና ሊድ ኮሚሽነሮች የተመደቡበት አሠራር ተዘርግቷል።
በምክክሩ ሂደት ዙሪያ የሚነሡ ትልልቅ የተሳሳቱ አመለካከቶች አንዱ “በአጀንዳዎች ላይ ድምፅ ብልጫ ተሰጥቶ ውሳኔ ሊወሰን ነው” የሚለው ነው። ዋና ኮሚሽነሩ እንዳረጋገጡት ግን፣ ምክክሩ የፖለቲካ ውሳኔ ማስተላለፊያ ወይም በድምፅ ብልጫ አሸናፊ እና ተሸናፊ የሚለይበት መድረክ አይደለም።
ይልቁንም የምክክሩ ዋና ውጤት ለሕግ አስፈፃሚው፣ ለሕግ አውጪው እና ለሕግ ተርጓሚው አካላት የሚተላለፉ ወሳኝ ምክረ-ሐሳቦች፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለሃይማኖት ተቋማት እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሰጡ አቅጣጫ ጠቋሚ ምክረ-ሐሳቦች ናቸው።
ስለሆነም ከውጭም ሆነ ከውስጥ “በውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ሎቢ እየተደረገ ነው” የሚባሉት አሉባልታዎች ከስሜት ያለፉ አይደሉም።
ምክክር ይጀመራል እንጂ በአንድ ጀምበር የሚያልቅ ባለመሆኑ፣ የመጡትን የ4 ሺህ ተመካካሪዎች ሐሳቦች አጠናቅሮ ለተግባሪ አካላት በማቅረብ እና አፈጻጸሙን በመከታተል ረገድ ረጅም ሥራዎችን ይጠይቃል።
ሂደቱ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች እኩል የሚደመጡበት እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ምክረ-ሐሳቦች የሚመነጩበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: