የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የዘመናት ልዩነት እና አለመግባባትን በሠለጠነ የመደማመጥ ምክክር ወደ የጋራ መግባባት እና የጋራ አሸናፊነትን የሚያቀዳጅ አካታች መድረክ መሆኑን ተመካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
በዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።
በመንግሥት አደረጃጀት እና ቅርጽ፣ በፖለቲካ ሥርዓት፣ በፖለቲካ ውክልና እና በምርጫ ሥርዓት፣ በሙስና እና በመልካም አስተዳደር፣ በሃይማኖት ጉዳዮች እና በሰላም ግንባታ አጀንዳዎች ላይ ተመካካሪዎች ባቀረቧቸው ምክረ ሐሳቦች መግባባት ላይ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ተመካካሪዎች እንዳሉት፣ ሀገራዊ ምክክሩ መደማመጥ እና መከባበርን መሠረት በማድረግ እየተካሄደ በመሆኑ የጋራ መግባባትን ለመገንባት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ተመካካሪ እና የጉምዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር ግራኝ ጉደታ እንደገለጹት፣ የምክክር ጉባኤው የጋራ መግባባትን በሚገነቡ አካታች እና አሳታፊ ሐሳቦች እየተንጸባረቁበት ነው።
ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወኪል ተመካካሪዎች ለሀገር የሚጠቅሙ የተለያዩ ሐሳቦችን በነጻነትበማቅረብ የጋራ ምክክር እየተካሄደባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ ለረጅም ዓመታት የቆዩ ችግሮችን ለመፍታትና ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሌላው ተመካካሪ እና የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት ሊቀመንበር ገብሩ በርኸ በበኩላቸው፣ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በውይይት የሚያምን ትውልድ እና ማኅበረሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ምክክር ለትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማሸጋገር የሚያግዝ የጋራ መድረክ ነው ያሉት አቶ ገብሩ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤም መግባባትን የሚገነባ ምክክር እያደረግን ነው ብለዋል።
ተመካካሪ ነስሩ ዑዳ በበኩላቸው፣ በጉባኤው የምንመክርባቸው ዐበይት አጀንዳዎች የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
በ10፣ በ50፣ በ250 እና በ500 የምክክር ቡድኖች ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው ምክክር መድረክ የጋራ መግባባትን የሚገነቡ ሃሳቦች እየቀረቡበት መሆኑን ገልጸዋል።
በምክክሩ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተመካካሪዎች ሰፊ ምክክር እያደረጉ እንደሚገኙም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የምክክር ሂደቱ አካታች እና አሳታፊ ነው ያሉት ተመካካሪዋ፣ ተመካካሪዎች የተለያዩ ሀሳቦችን በመከባበርና በመደማመጥ በማንሳት የጋራ መግባባት የሚገነባ ምክክር እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: