Search

የጠረጴዛ ዙሪያው ድል፡ ኢትዮጵያውያን ሲመክሩ የማይፈታ ዕንቆቅልሽ እንደሌለ ያመላከተ ታሪካዊ ምዕራፍ

ረቡዕ ነሐሴ 06, 2018 37

በፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ በርካታ ስብራቶች የነበሩ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን በጠረጴዛ ዙሪያ በነፃነት ከተሰባሰቡ፤ ሁሉንም ችግሮች በአንድ ጊዜ መፍታት ባይቻልም፣ መነጋገሩ እና የጋራ መፍትሔ መፈለጉ በራሱ ትልቅ ድል መሆኑን አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በተግባር እያሳየ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ ያገኘችውን ይህን ወርቃማ የፖለቲካ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ለቀጣይ የሀገር ግንባታ ፅኑ መሠረት መጣል እንደሚቻል የጉባኤው ሂደቶች ፍንትው አድርገው እያሳዩ ነው።

ከኃይል አማራጭ እና ከጽንፈኝነት አዙሪት ወጥቶ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት የተደረገው ይህ ሽግግር ዜጎች በገዛ ጉዳያቸው ላይ ሲመክሩ የሚያመጡትን አስደናቂ የመቀራረብ እና የመግባባት ውጤት እያንጸባረቀ ነው።

በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ከሁሉም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የተወጣጡ 4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች በአንድነት ተሰባስበዋል። ይህ ስብስብ ወጣቱን፣ ሴቱን፣ የፖለቲካ ልሂቃኑን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ያቀፈ በመሆኑ ለውሳኔዎቹ ልዩ ሀገራዊ ክብደት ሰጥቶታል።

የመግባባት ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን የተዘረጋው ሳይንሳዊ አደረጃጀት እጅግ አስደናቂ ነው። በአስር አባላት ከተዋቀሩ 400 ንዑሳን የውይይት ቡድኖች ጀምሮ፣ 50 250 እንዲሁም እስከ 500 አባላት እስካሏቸው ስምንት የምክክር ቡድኖች ድረስ እጅግ ሰፊ የሐሳብ ማጥራት ሥራ ተከናውኗል።

ይህንንም ውስብስብ ሂደት 160 ገለልተኛ አመቻቾች እና 256 የቃለ ጉባኤ ጸሐፊዎች በከፍተኛ የሙያ ብቃት መርተውታል። ይህ ጥበብ የተሞላበት አካሄድ የሚያረጋግጥልን አንድ ትልቅ እውነት አለ፤ እርሱም ቀደም ሲል የነበሩን አለመግባባቶች መንሥኤ የልዩነቶቻችን ግዝፈት ሳይሆን ሐሳቦችን በነፃነት አዳብሮ ወደ መፍትሔ የሚያሸጋግር ገለልተኛ መድረክ ማጣታችን መሆኑን ነው።

ኢትዮጵያን በማስቀደም በጋራ መመካከር ከተቻለ መግባባት የማይቻልባቸው አጀንዳዎች እንደሌሉ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ማሳያ ነው።

በተለይም ስምንት ዐበይት አጀንዳዎችን ይዘው ሲወያዩ ከነበሩት ቡድኖች መካከል አራቱ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሙሉ መግባባት ላይ ደርሰው በቃለ ጉባኤ ሰነዶቻቸው ላይ በይፋ መፈራረማቸው የምክክሩን ፍሬያማነት ያበሰረ ሆኗል።

በእነዚህ 500 አባላት ባሏቸው አራት ቡድኖች የተደረሰባቸው ስምምነቶች ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ውጥረት መንሥኤ በነበሩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ የተመሠረቱ ናቸው።

የመጀመሪያው ቡድን በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ የመከረ ሲሆን ተቋማቱ ስላላቸው አብሮነት፣ ነፃነት እና ለሀገር ግንባታ ስለሚያበረክቱት በጎ አስተዋጽኦ ሙሉ ስምምነት ላይ ደርሷል።

በተመሳሳይ የሰላም ግንባታው ቡድን የግጭት መንሥኤዎችን እና አፈታታቸውን ነቅሶ በማውጣት፣ የዘላቂ ሰላም መሠረቶችን ከባህላዊ ዕርቅ እና ይቅርታ ጋር በማስተሳሰር የጋራ አቋም ይዟል።

በሌላ በኩል እጅግ ውስብስብ ተደርገው ይወሰዱ በነበሩት የመንግሥት ቅርጽ፣ የፌዴራሊዝም አተገባበር፣ የሥልጣን ክፍፍል፣ የፖለቲካ ውክልና እና የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ጉዳዮች ላይ የመከረው ቡድንም ሰፊ ውይይት በማድረግ ታሪካዊ ስምምነት አድርጓል።

አራተኛው የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቡድንም፣ ፀረ ሙስና ሥርዓትን ስለመገንባት እና ፍትሐዊ የሕዝብ አገልግሎት (ፓብሊክ ሰርቪስ) አደረጃጀትን በተመለከተ በሙሉ ድምጽ አቋሙን አጽድቋል።

እነዚህ በነፃነት የተደረሱ ተጨባጭ የቃለ ጉባኤ ስምምነቶች ወደ ሕጋዊ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች ሲቀየሩ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ መዋቅር እንደ አዲስ የመቃኘት እና የማደስ ከፍተኛ አቅም አላቸው።

ከዚህም ባሻገር በሂደቱ የታየው የመደማመጥ እና የመከባበር መንፈስ በዜጎች መካከል ለዘመናት የቆየውን የጥርጣሬ ግንብ በማፍረስ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ የመፍታት ባህል እየጎለበተ መምጣቱ ማሳያ ነዉ።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ይህንን ወርቃማ የሰላም እና የምክክር ዕድል በጥንቃቄ ወደ ተግባር ከቀየሩት ሀገራችንን ከተረከበችው የፖለቲካ ስብራት በማውጣት በትልቁ የብልጽግና እና የአንድነት ከፍታ ላይ እንደሚያስቀምጧት የተጀመሩት ተስፋ ሰጪ ስኬቶች በግልጽ ይመሰክራሉ።

የውይይት ጠረጴዛው አሸንፏል፤ የጋራ መግባባት በሩን ወለል አድርጎ ከፍቷል!

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: