Search

ከብረት የጠነከረው የአንበሳ ልብ፡ የኢትዮጵያ ወታደር ፅናት እና ተቋማዊ ጥንካሬ

ረቡዕ ነሐሴ 06, 2018 80

በወታደራዊ ሳይንስ ጥናት ውስጥ የአንድ ጦር አቅም የሚለካው በታጠቀው የብረት መሣሪያ ጥንካሬ ወይም በሠራዊቱ አኃዛዊ ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በወታደሩ ደረት ውስጥ በሚነድደው የሀገር ፍቅር እሳት እና በማይበገረው የሥነ-ልቦና ፅናት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) "አንድ ነገር በእርግጠኝነት የምናገረው ግን የኢትዮጵያ ወታደር ያለውን ዓይነት ልብ ማንም የለውም" በማለት የገለጹት ሐሳብ፣ ይህንን የታሪካዊ ዐርበኝነታችንን ጥልቅ ዐሻራ እና የሠራዊቱን መንፈሳዊ ልዕልና ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

ይህ የማይበገር ልብ የተገነባው ለዘመናት በወረራዎች፣ በሕልውና ፈተናዎች እና በከበዱ መሥዋዕትነቶች ውስጥ በማለፍ በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ ነፃነት እና ክብር ዋስትና ሆኖ የዘለቀ ታላቅ ተቋማዊ ሀብት ነው።

የኢትዮጵያ ወታደር የውጊያ ባሕሪ እና የታክቲክ ብስለት በግልጽ የሚታየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጠቀሙት እና የሠራዊቱን ሥልታዊ ጥልቀት በሚያሳየው አገላለጽ ነው፤ "የኛ ወታደር ሲያጠቃ እንደ ተኩላ ሲከላከል እንደ አንበሳ ነው" በማለት።

ሠራዊቱ የጠላትን አሰላለፍ ሰብሮ ለመግባት በሚንቀሳቀስበት ወቅት እንደ ተኩላ በከፍተኛ ቅንጅት፣ በፈጣን የቡድን ጥቃት እና ዒላማውን በጠበቀ ሥልታዊ ጥበብ ጠላቱን ድባቅ ይመታል።

የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እና የሕዝቧን ሕልውና ለማስጠበቅ በሚቆምበት ጊዜ ደግሞ፣ እንደ አንበሳ ማንም ሊደፍረው በማይችለው ጠንካራ ምሽግ እና አይበገሬነት ፀንቶ በመቆም ኢትዮጵያን በክፉ ሲያስብ የመጣን ኃይል ሁሉ እንድርድ ያደርገዋል።

ይህ ሥልታዊ ተለዋዋጭነት ወታደሩ በውጊያ ሜዳ ላይ የሚጎናጸፈው የብቃት እና የልብ ፅናት ማረጋገጫ ነው።

ከዚህ የልብ ፅናት ባለፈ የዘመኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪካዊ ጀግንነቱን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር አዋህዶ የላቀ አቅም ፈጥሯል።

በተደረገው ተቋማዊ ሪፎርም ሠራዊቱ በዘመናዊ የድሮን ቴክኖሎጂ፣ በአየር ኃይል ሥምሪት እና በሳይበር ደኅንነት ራሱን በሚገባ በማስታጠቅ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ወደር የማይገኝለት ኃይል መሆን ችሏል።

በባዶ እግራቸው ዓድዋ ላይ ታሪክ የሠሩት አባቶቻችን የጀግንነት ወኔ፣ ዛሬ በዘመናዊ የጦር ትጥቅ እና በመረጃ ትንተና አቅም ተደግፎ ኢትዮጵያን ከማንኛውም የውጭ ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ እየጠበቀ ይገኛል።

ይህ ከብረት የጠነከረ ልብ ኢትዮጵያ ላይ ከአንዣበቡ የጥፋት ደመናዎች እና የውጭ ጠላቶች ሤራ እንዴት እየታደጋት ይገኛል ከተባለ፣ መልሱ በቅርብ ዓመታት በተካሄዱ የሕልውና ማስከበር ዘመቻዎች እና በታሪክ ምዕራፎቻችን ውስጥ በጉልህ ተጽፎ ይገኛል።

ከዓድዋ ተራሮች እስከ ካራማራ፣ ከባድመ እስከ አሁናዊ የሉዓላዊነት ማስከበር ስኬቶች ድረስ ሠራዊቱ ማንኛውንም ፈተና አልፎ ድል የተቀዳጀው በውስጡ ባለው የማይነጥፍ የሀገር ፍቅር እሳት ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የሠራዊቱ ልብ በውጊያ ሜዳ በሚያሳየው ግርማ ሞገስ ብቻ የሚገደብ ሳይሆን፣ በሰላም ጊዜ በሚያሳየው ጥልቅ ሰብዓዊነት እና ርኅራኄ የተሞላ ነው።

በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን እና በአብዬ የተካሄዱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ የኢትዮጵያ ወታደር ያሳየው ሰብዓዊ አቀራረብ እና የሕዝብ ጥበቃ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን አትርፎለታል።

በአሁኑ ወቅትም ይህ ሠራዊት ድንበር ከመጠበቅ ባለፈ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ብሔራዊ የልማት አውታሮችን ሌሊት ከቀን ነቅቶ በመጠበቅ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እና የብልፅግና ጉዞ በፅናት ደግፎ ይዟል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ የሚውለበለበው፣ የነፃነት ታሪካችን ተከብሮ የሚኖረው በዚህ ከብረት በጠነከረ የወታደሮቻችን የማይበገር ልብ እና በጽኑ ተቋማዊ መሠረት ላይ ነው።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: