የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነት የተገዙ 232 ሞተር ሳይክሎችን ለክልሎች ማስረከቡን አስታወቀ።
እነዚህ ተሽከርካሪዎች በሰባት ክልሎች ለሚገኙ 116 ወረዳዎች የሚከፋፈሉ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ወረዳ ሁለት ሞተር ሳይክሎችን የሚያገኝ ይሆናል።
ድጋፉ በቆላማ አካባቢዎች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን እና የመስክ እንቅስቃሴዎችን ለማቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ይገዙ፣ የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በመጀመሪያው ምዕራፍ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ በታቀደው ልክ ውጤታማ በመሆኑም ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
አክለውም በዛሬው ዕለት ለክልሎች የተላለፉት ሞተር ሳይክሎች የቆላማ አካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግና ሥራዎችን በፍጥነት ለማከናወን እንደሚያግዙ አስረድተዋል።
ክልሎችም ተሽከርካሪዎቹን ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ እንዲያውሉ እና አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የክልል ተወካዮች በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ ያጋጥም የነበረውን የተሽከርካሪ እጥረት በመቅረፍ ሥራዎችን በተሻለ ፍጥነት ለማከናወን እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
በአባዲ ወይናይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: