Search

በአጀንዳ ማጠናቀር ሂደቱ ለሀገራችን የተሻለ ሐሳብ ይዞ መውጣት እንደሚቻል ተገንዝበናል - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

ረቡዕ ነሐሴ 06, 2018 85

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አጀንዳዎችን የማጠናቀር ሂደት በተቀመጠው አቅጣጫ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከንዑሳን ቡድኖች የመጡት አጀንዳዎች 500ዎቹ ተወካዮች መቅረባቸው እንደቀጠለ ዋና ኮሚሽነሩ ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

በእነዚህ 500 ተወካዮች ውስጥ ከሚገኙት መካከል በአራቱ ቡድኖች ላይ የቀረቡ አጀንዳዎች በትናንትናው ዕለት ሙሉ በሙሉ ስምምነት የተደረሰባቸው ሲሆን፣ ዛሬም መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ እንዳብራሩት፣ ስምምነት ላይ ተደረሰ ሲባል መቶ በመቶ በሁሉም ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ መግባባት ተፈጠረ ማለት ሳይሆን በአጠቃላይ አቅጣጫው እና ሂደቱ ላይ የጋራ መግባባት ተይዟል ማለት ነው።

ተሳታፊዎች የየራሳቸው ልዩ ጉዳይ በዝርዝር እንዲጠቀስ ፍላጎት ቢያሳዩም፣ አሠራሩ አንዱን ሐሳብ በሌላው ውስጥ በማጠቃለል አብዛኛውን የሚወክል የጋራ አጀንዳ መፍጠር መሆኑ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ከተመካካሪዎች ውጭ ያሉ ማናቸውም አካላት በምንም መልኩ በተወካዮቹ ሐሳብ ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ይገኛል።

በዚህ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ ቅሬታዎች እና ኩርፊያዎች መከሰታቸው የሚጠበቅ መሆኑን ያነሡት ፕሮፌሰር መስፍን፣ ኮሚሽኑ እነዚህን ችግሮች በየደረጃው እየፈታ እንደሚሄድ አረጋግጠዋል።

በሂደቱ የሐሳብ ግጭቶች ሊኖሩ ቢችሉም ምንም የሚያስፈራ ነገር እንደሌለ እና በተሻሻለ መግባባት ላይ በመድረስ ለሀገራችን የተሻለ ሐሳብ ይዞ መውጣት እንደሚቻል አመላክተዋል።

ውይይቱ አሁን ባለበት አበረታች ሁኔታ ከቀጠለ ከሳምንቱ መጨረሻ በፊት በዋና ዋና የምክረ ሐሳብ መነሻዎች ላይ ጠንካራ መግባባት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ተጠቁሟል።

በመቀጠልም መግባባት የተደረሰባቸው እና የጠሩ ጉዳዮች 4 ሺህዎቹ ተሳታፊዎች የሚቀርቡ ይሆናል።

በመሐል ጥያቄ የሚነሣባቸው ጉዳዮች ካጋጠሙ ደግሞ፣ ተመካካሪዎች በራሳቸው በመረጧቸው የክልል ጉባኤ አጣሪዎች፣ የሽማግሌዎች ስብስብ እና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በኩል ቀርበው ተገቢው መፍትሔ እንደሚሰጣቸው ኮሚሽኑ አሳውቋል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: