Search

የወሎ ተርሸሪ ኬር እና ማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ - ዛሬም በአዲስ ተስፋ

Aug 18, 2025

ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የወሎ ተርሸሪ ኬር እና ማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ ለ13 ዓመታት ተጓትቷል። ይህንን ጉዳይ ኢቢሲ በየጊዜው እየተከታተለ ሲዘግበውም ቆይቷል።
አሁን ላይ የሆስፒታሉን ግንባታ ገንዘብ እና ንብረት የፌደራል እና የክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የደቡብ ወሎ ዞን እና የደሴ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት በተገኙበት ወሎ ዩኒቨርስቲ ተረክቧል።
ከሕዝብ የተሰበሰበውን 95 ሚሊዮን ብር ገንዘብ በይፋ የተረከቡት የወሎ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችም ግንባታውን ግብ ለማድረስ ቃል ገብተዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ገንዘቡን የተረከበው ከወሎ ተርሸሪ ኬር እና ማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ ማስተባበሪያ የበጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑም ታውቋል።
በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ዩኒቨርሲቲው የተረከበው ግንባታ ከግብ እንዲደርስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የደሴና አካባቢው ከተማ ነዋሪዎች ለሆስፒታሉ ግንባታ ከአሁን በኋላ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ዋነኛ ኃላፊነት እንዳለበት ለኢቢሲ ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ ነዋሪው አቶ በየነ ፈንታው ፤ የሆስፒታሉ ግንባታ እጅግ በመዘግየቱ ገንዘቡ ጠፍቷል የሚል ሃሳብ በሕዝብ ዘንድ ይነሳ እንደነበር አስታውሰዋል።
ኢቢሲም ይህን ጉዳይ ይዞ በየጊዜው በመስራት እየተከታተለው መሆኑን አንስተው፤ አሁን ተመልሶ የሆስፒታሉ ግንባታ ጉዳይ ወደዩኒቨርሲቲው በመምጣቱ ደስ ብሎኛል ብለዋል።
ሌላኛው የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ ከበደ ወ/ሩፋኤል በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ ግንባታ ጉዳይ የሕዝቡ ቁጭት ከፍተኛ ነው፤ አሁን ወደግንባታው የሚመለስ ከሆነ ልዩ ደስታ ነው የሚፈጥረው ሲሉ ተናግረዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከአሁን በኋላ ሕዝብ የጣለበት አደራ ከፍተኛ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ይህንን አደራ በአግባቡ በመወጣት ለበርካታ ሕዝብ አገልግሎት የሚሰጠውን ግዙፍ ሆስፒታል ለማጠናቀቅ በትጋት መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉ ከአደራ ጭምር ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
በሆስፒታሉ ግንባታ ጉዳይ ለሚነሳው የሕዝብ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ዩኒቨርሲቲው የተቀበለውን ትልቅ ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ነው የገለጹት።