ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን የትብብር መስክ ጠንካራ መሰረት የጣሉ ሀገራት ናቸው።
በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም እና በሰዎች ለሰዎች ግንኙነት ትስስራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዱ ውይይቶችንም በተደጋጋሚ ተደርገዋል።
በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ ለመቅሰም እና የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ያተኮሩ ሥዎችን ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት እንደምትፈልግ የፓኪስታን የሥራ ሃላፊዎች እየገለጹ ይገኛል።
የሀገሪቱ ሴኔት መሪ እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዩሱፍ ራዛ ጌላኒ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ትግበራ ባመጣችው ለውጥ ፓኪስታን በዓለም መድረክ ስትራቴጂያዊ አጋሯ አድርጋ እንደምትሠራ ተናግረዋል።
ይህ ሃሳብ እንዴት መጣ ቢሉ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖው እየጎላ ያለው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ትግብራ ውጤት ነው ብሎ መውሰድ እንደሚቻል ይነሳል።
ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ውጤት ያመጣውን የአረንጓዴ ዐሻራ በማስፋፋት ለአረንጓዴ
ዲፕሎማሲ ትግበራ እየተጠቀመችበት ስለመሆኑም በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ባሰናዳው መድረክ ላይ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ለኢቢሲ ተናግረዋል።
ፓኪስታን በኢትዮጵያ እየተሰራ ያለው ሥራ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን በተፈጥሯዊ መንገድ መፍትሄ ያበጀ መሆኑ በሚገባ ተገንዝባለች ሲሉ አምባሳደሩ አንስተዋል።
አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የጀመሩትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር በዓለም መድረክ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ የትብብር ሥራዎችን እንደምትሰራ የሀገሪቱ ሴኔት መሪ እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዩሱፍ ራዛ ጌላኒ መግለጻቸው በጋራ የሚከናወኑ የአረንጓድ ልማት ሥራዎችን ለማጠናከር እንደሚረዳም አንስተዋል።
በሄለን ተስፋዬ
#EBC #ebcdotstream #GreenLegacy