የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ያለፈው የካቲት ወር ላይ ካደረጉት የነጩ ቤተመንግስት ውይይት ይልቅ የዛሬው ሰላም የሰፈነበት እና በእርጋታ የተሞላ እንደነበር በርካታ የዓለም መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ይገኛል።
በፈገግታ የታጀበው ውይይት ዋና ትኩረቱ ሰላም ነበር፤ ቮሎድሚር ዜለንስኪ ያለፈው ጊዜ ወደነጩ ቤተመንግስት ሲመጡ የተወቀሱበትን አለባበስ ቀይረው ተገኝተዋል።
የተለመደው ሹራብ እና ቀለል ያለ አለባበስን አድረገው ሳይሆን ኮት ደርበውም ነበር በውይይቱ ላይ የታዩት።
ዶናልድ ትራምፕም እንግዳቸውን በክብር ከተቀበሏቸው በኋላ ተወያይተዋል።
በነጩ ቤተ-መንግስት ከቮሎድሚር ዜለንስኪ ጋር ባደረጉት ውይይትም ዩክሬን የኔቶ አባል የመሆን ፍላጎቷን መተው እንደሚገባት ግልጽ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ እና ዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ሳይሆን ዘላቂ የሰላም ነጥቦችን በማስቀመጥ ከስምምነት እንዲደርሱ በማድረግ ሂደት ላይ አሜሪካ እንደምትሳተፍ ገልፀዋል፡፡
ይህ እንዲሆንም ዩክሬን የኔቶ አባል ለመሆን ያላትን ፍላጎት መተው እንዳለባት አስታውቀዋል፡፡
ዜለንስኪ በበኩላቸው ከየትኛውም ስምምነት በፊት የደህንነት ዋስትና ለሀገራቸው እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና እንደሚሰጡ የገለፁት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የሚቀመጡ የስምምነት ነጥቦች በሩሲያ የሚጣሱ ከሆነ በጦርነቱ አሜሪካ በቀጥታ ተሳታፊ ልትሆን እንደምትችል ጠቆም አንድርገዋል።
እንዲሁም ከዚህ ቀደም በዩክሬን ዲሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ መካሄድ አለበት የሚው ሃሳባቸውን ጦርነቱ እስከሚያበቃ ድረስ ማዘግየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይህን የትራምፕ ሃሳብ ያደነቁት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጥሩ ውይይት መደረጉን ነው የገለጹት።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በቀጣይ ከሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ጋር በድጋሚ እንደሚገናኙ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎችም በአሜሪካ ነጩ ቤተመንግስት ተገኝተዋል።
በአፎሚያ ክበበው
#EBC #ebcdotstream #usa