Search

የኢትዮጵያ ብዝኃ ኢኮኖሚ ልማት ዕድገትን የሚያፋጥን አስደማሚ ውጤት እያመጣ ነው - ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ምሁራን

እሑድ ነሐሴ 10, 2018 72

 

የኢትዮጵያ ብዝኃ የኢኮኖሚ ልማት ዕድገትን የሚያፋጥን አስደማሚ ውጤት እያመጣ መሆኑን የአሜሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ምሁራን ገለጹ።

አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ሚጉኤል እና ካሜሩናዊው የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ሊነስ ኒውል እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች አስደናቂ ዕድገት እና ለውጥ አስመዝግባለች።

በአሜሪካ የካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ሚጉኤል፣ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ በአዲስ አበባ የተመለከቱት ለውጥ እጅግ የሚያስደምም መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ አስደናቂ የከተሜነት ዕድገት እና የልማት ለውጥ ከዚህ ቀደም ያውቋቸው የነበሩ አካባቢዎችን ገጽታ በእጅጉ በመቀየሩ እንደገና ለመለየት እንኳን እንደተቸገሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለከተማ መሠረተ ልማት የሰጠው ልዩ ትኩረት የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል።

በከተማ ልማት፣ በኢኮኖሚ ማሻሻያና በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የተመዘገቡ ውጤቶች የኢትዮጵያን የልማት ቁርጠኝነት የሚያሳዩ አስደናቂ ስኬቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በብዝኃ ኢኮኖሚ ዘርፎች የወሰደቻቸው የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎችም ዕድገትን በማፋጠን አዎንታዊ ውጤት እያመጡ እንደሚገኙ አንስተዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ረገድም ኢትዮጵያ አዳዲስ የማኅበራዊ ፕሮግራሞችንና የፋይናንስ አሠራሮችን በመዘርጋት የመቋቋም አቅሟን ለማሳደግ የወሰደቻቸው እርምጃዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አፍሪካ ለድርቅ እና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆነችበት በዚህ ወቅት የመንግሥት ቁርጠኝነትና በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በአሜሪካ ፔንሲልቬኒያ ጌቲስበርግ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ ምሁር የሆኑት ካሜሩናዊው ፕሮፌሰር ሊነስ ኒውል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች አስደናቂ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የወሰደቻቸው አስደናቂ የልማት መርሃ ግብሮችም የሀገሪቱን ዕድገት ከማፋጠን ባሻገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ አቅሞችን ለመገንባት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት እያስመዘገበች ያለችው እመርታም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር የሚተርፉ ወሳኝ ተሞክሮ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ መንግሥት በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና መቋቋም ውጤታማነቱን በማሳደግ፣ አህጉራዊ የምሪት ሚናዋን አጠናክራ ልትቀጥል እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: