በኢትዮጵያ እውን እየሆነ ያለው ሀገራዊ ምክክር ለዘመናት የሕዝብ ብሶቶች እና ጥያቄዎች እንዲሁም ለታሪክ ስብራቶች በሰለጠነ መንገድ እልባት ለመስጠት ያለመ አዲስ ልምምድ ነው።
በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አመለካከቶችን ይዞ ወደ ውይይት ጠረጴዛ በመምጣት በእኩልነት መምከር መቻል በራሱ ትልቅ ታሪካዊ ስኬት ነው።
እንዲህ ያለው አካታች ምክክር ከዚህ ቀደም ለተነሱ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ሊነሱ ለሚችሉ የማኅበረሰብ ጥያቄዎች ዘላቂ እና አስተማማኝ ምላሽ የሚገኝበት ዋነኛ መንገድ ነው።
ምክንያቱም እውነተኛና ዘላቂ መፍትሔ የሚወለደው ሁሉን ወገኖች በማካተት ከሚደረግ የሰከነ ውይይት እንጂ ከታጣቂዎች አፈሙዝ ሊሆን አይችልም።
በሀገራዊ ምክክራችን ሂደት በተለያዩ አጋጣሚዎች ከተለያዩ አካላት የሚሰነዘሩ ከእውነታ የራቁ አሉባልታዎች እና አሉታዊ ሀሳቦች ወደ ዘላቂ ሰላም የጀመርነውን ጉዞ ሊያስተጓጉሉት አይችሉም።
እነዚህ አሉባልታዎች እና አሉታዊ ሀሳቦች የሕዝቡን ፍላጎት የማይወክሉ፣ ይልቁንም የሰላም ሂደቱን ለማስተጓጎል እና ጥርጣሬን ለመዝራት የሚደረጉ ከንቱ መፍጨርጨሮች ናቸው።
ከእልቂት እና ከውድመት በቀር ከጦርነት እና ከጽንፈኝነት ያተረፍነው አንዳች ጥቅም እንደሌለ ያለፈው ታሪካችን ሕያው ምስክር ነው።
በመሆኑም ከብጠመንጃ ይልቅ አሁን የጀመርነው የሰለጠነ የምክክር መንገድ ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ ብቸኛው አማራጭ ነው።
ሀገር የምትመራው እና የምትገነባው በሰከነ ውይይት እና በሕግ ጽኑ መሠረት ላይ እንጂ በኃይል እና በጠመንጃ አይደለም።
አሁን እያካሄድነው ያለው ሀገራዊ ምክክር የረጅም ሂደት ጅማሮ እንጂ መዳረሻው አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ምክክሩ ወደፊትም ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ኃይሎች እያሳተፈ፣ ድምጻቸው እንዲሰማ እያደረገ በተደራጀ እና በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል።
ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም የመፍትሔው አካል የሚሆንበት በመሆኑ፣ ለነገዋ ሰላማዊት እና የበለጸገች ኢትዮጵያ ጠንካራ መሠረት እየጣለ ይገኛል።
ምክክሩ ለዛሬ ሰላማችን የምንጠቀምበት ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ትውልድ ጭምር በቅርስነት የሚተላለፍ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ነው።
በሰከነ ሀገራዊ ምክክር ከግጭት አዙሪት በመውጣት ለቀጣዩ ትውልድ ሰላም እና አንድነቷ የተጠበቀ የበለጸገች ኢትዮጵያን ከሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ጋር እናስረክባለን።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: