በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የአፍሪካ አህጉር በአውሮፓ ኃያላን የቅኝ ግዛት ሽሚያ እጅግ ፈታኝ በሆነ የታሪክ ማዕበል ውስጥ ስትላጋ፣ የኢትዮጵያ ህልውና በከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር።
በተለይም የኢትዮጵያ የትንፋሽ ቱቦ የሆነው የቀይ ባሕር ዳርቻ እና የምጽዋ ወደብ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያን፣ እንዲሁም የግብፅ የጥቅም ግጭት ማዕከል ሆኖ ይመሰቃቀል ነበር።
በዚህ እጅግ ውስብስብ፣ አደገኛ እና አሻጥር በበዛበት የዓለም አቀፍ ፖለቲካ መድረክ ላይ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ከውጭ ወራሪዎች ለመከላከል እንደ ትልቅ ዋርካ ጸንተው የቆሙት ታላቁ ዐርበኛ እና የጦር ጄኔራል ራስ አሉላ አባነጋ ነበሩ።
የሀገር ድንበር ከባሕር እንደሚጀምር በሚገባ የተገነዘቡት እኚህ ታላቅ የጦር ጠቢብ ሙሉ ሕይወታቸውን የሰሜኑን በር በመጠበቅ እና ወራሪዎችን በማርበድበድ አሳልፈዋል።
የግብፅን ትንኮሳ መመከት፡ የጉንደት እና የጉራዕ አንጸባራቂ ድሎች
የራስ አሉላ አባነጋ የጀግንነት እና የሀገር ፍቅር ታሪክ የሚጀምረው አውሮፓውያን ቀይ ባሕርን ከመቆጣጠራቸው አስቀድሞ፣ በቀጣናው ሰፊ የቅኝ ግዛት ህልም ሰንቃ የነበረችውን የግብፅን ወረራ በመመከት ነው።
በ1868 ዓ.ም ግብፆች ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ስር ለማድረግ አስበው በአውሮፓውያን እና በአሜሪካውያን የጦር መኮንኖች የሚመራ እጅግ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀ ጦር በምጽዋ በኩል ወደ መሀል ሀገር ላኩ።
ይህ ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ደፍሮ ሲገባ በወቅቱ ሻለቃ የነበሩት አሉላ አባነጋ በኅዳር ወር 1868 ዓ.ም በጉንደት ጦርነት ላይ የግብፅን ጦር አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ወደር የለሽ ጀግንነትን ፈጸሙ።
ራስ አሉላ በፈጠሩት አስደናቂ ወታደራዊ ታክቲክ የግብፅ ጦር አዛዥ የነበረው ዴንማርካዊው ሶረን አረንድሩፕ ተገደለ፤ ጦሩም ሙሉ በሙሉ ተደመሰሰ።
የግብፅ መንግሥት በጉንደት የተከናነበውን ውርደት ለመበቀል በማሰብ በዚያው ዓመት (በየካቲት 1868 ዓ.ም.) በድጋሚ በከፍተኛ ዝግጅት በራቲብ ፓሻ እና በአሜሪካዊው ጄኔራል ሎሪንግ የሚመራ ከበፊቱ የገዘፈ ጦር ይዞ በጉራዕ ላይ ዘመተ።
ታዲያ በዚህ እጅግ ወሳኝ በሆነ የህልውና ጦርነት ላይ ራስ አሉላ የዐፄ ዮሐንስን ጦር በግንባር ቀደምትነት በመምራት የግብፅን ሠራዊት ድል አደረጉ።
በጉራዕ ሜዳ ላይ የግብፅ ጦር የፈረሰበት እና ከፍተኛ የጦር መሳሪያ የተማረከበት የራስ አሉላ ወታደራዊ ጥበብ የኢትዮጵያን ሰሜናዊ ድንበር ከግብፅ ስጋት ሙሉ በሙሉ ነጻ ያወጣ ነበር።
ለዚህ ውለታቸው እና ለግሩም አመራራቸው ዐፄ ዮሐንስ "ራስ" የሚለውን ማዕረግ ሸልመው የመረብ ምላሽ (የአሁኗ ኤርትራ) አስተዳዳሪ አድርገው ሾሟቸው።
የቀይ ባሕር አደራ እና የመረብ ምላሽ አስተዳደር
ራስ አሉላ አባነጋ እጅግ ፈታኝ እና ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለውን የሰሜን ድንበር ግዛት (መረብ ምላሽን) እንዲያስተዳድሩ ሲሾሙ ኃላፊነታቸው የኢትዮጵያን የባሕር በር ከውጭ ጠላቶች የመጠበቅ፣ ጠላት ድንበር ጥሶ ወደ መሀል ሀገር እንዳይገባ እንደ ጸና ዓለት የመቆም ታላቅ ሀገራዊ አደራ ነበር።
በዚህ ታላቅ ኃላፊነታቸው ዘመን፣ ራስ አሉላ የመንግሥታቸውን ማዕከል ወደ አሥመራ በማዛወር ከተማዋን በከፍተኛ ደረጃ አስፋፉ።
ወታደራዊ ሎጂስቲክስን እና ፈጣን የጦር እንቅስቃሴን ታሳቢ በማድረግ፣ ከአሥመራ ወደ ምጽዋ የሚወስደውን አሮጌ እና አደገኛ የተራራ መንገድ በማስፋት ለፈረሰኛ ጦር እና ለመድፍ ማጓጓዣ ምቹ እንዲሆን አድርገው አሠርተዋል።
ይህ እርምጃቸው የባሕር በሯን ደኅንነት በቅርበት ለመቆጣጠር እና ጠላት ከምጽዋ ወደ ምድር ሀገር የሚያደርገውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ በአጭሩ ለመቅጨት ያስቻላቸው ታላቅ የስትራቴጂ ሊቅነታቸውን የሚያሳይ ነበር።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የደም ስር የሆነው ቀይ ባሕር፣ በአሉላ ንቁ ዓይኖች ስር ወደር የለሽ ጥበቃ ተደርጎለታል።
የሂዊት ውል፡ ለኢትዮጵያ የባሕር በር የተከፈለ ደም
በ1870ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ በሱዳን የተቀሰቀሰውን የደርቡሽ አመጽ ተከትሎ የተከበቡትን የግብፅ ወታደሮች በሰላም ለማስወጣት እንግሊዝ የኢትዮጵያን እርዳታ ጠየቀች።
በዚህም መሠረት ግንቦት 26 ቀን 1876 ዓ.ም በዓድዋ ከተማ በተፈረመው የሂዊት ውል፣ ኢትዮጵያ የግብፅ ወታደሮችን በግዛቷ አቋርጠው በሰላም በማስወጣት ምትክ ግብፆች በኃይል ይዘውት የነበረው የቦጎስ ግዛት እንዲመለስላት እና በምጽዋ ወደብ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነጻ በነጻነት እንድታስገባ ተስማማች።
ራስ አሉላም ይህንን ስምምነት በማክበር በኩፊት ጦርነት ላይ የደርቡሽን ጦር በጀግንነት ደምስሰው የራሳቸውን ወታደሮች ደም አፍስሰው የግብፅ ወታደሮችን በሰላም ምጽዋ በማድረስ የሀገራቸውን ቃል ኪዳን በተግባር ጠበቁ።
የታሪክ ክህደት እና የአሉላ የነበልባል ቁጣ
ሆኖም ግን የአውሮፓውያን የፖለቲካ ተንኮል እና እምነት ማጉደል ድንበር የለሽ ነበር። እንግሊዞች የገቡትን ዓለም አቀፋዊ ቃል በግልጽ በማጠፍ፣ የፈረንሳይን የጂቡቲ መስፋፋት ለመግታት እና የቀይ ባሕርን ስትራቴጂያዊ የበላይነት የራሳቸው አሻንጉሊት በሆነ ኃይል ሥር ለማድረግ ሲሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ የባሕር በር የሆነችውን ምጽዋን የካቲት 1877 ዓ.ም ታዳጊ ለነበረችው የጣሊያን ኃይል አሳልፈው ሰጡ።
ይህ የእንግሊዞች ፀያፍ የዲፕሎማሲ ክህደት ራስ አሉላን እጅግ አስቆጣቸው። አሉላ የአውሮፓውያንን በሁለት ቢላዋ (Double standard) እና ተንኮል በጥልቀት ተረዱ።
ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የባሕር በር በውል እና በወረቀት ሳይሆን፣ በብረት እና በደም ብቻ እንደሚጠበቅ ቆርጠው ተነሱ። ጠላት ምጽዋ ላይ መሽጎ ወደ መሀል ሀገር ለመዝለቅ ሲያደባ፣ ራስ አሉላ እንደ ነበልባል እሳት ሆኑባቸው ።
የጣልያንን መስፋፋት መግታት፡ ከአይለት እስከ ታላቁ የዶጋሊ ድል
ጣልያኖች ምጽዋን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ቀስ በቀስ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ለመስፋፋት ሙከራ ማድረግ ጀመሩ። በ1879 ዓ.ም ሣሃጢ እና ዋዓ በተባሉ ቦታዎች ምሽግ ሠርተው ድንበር ሲጥሱ፣ ራስ አሉላ ወዲያውኑ የመብረቅ ያህል በፍጥነት እርምጃ ወሰዱ።
መጀመሪያ አይለት በተባለ ቦታ ላይ የጣልያንን ጦር በድንገት በማጥቃት ኃይላቸውን አሽመድምደው ጠንካራ መልዕክት አስተላለፉ።
ራስ አሉላ ለጣሊያን ጄኔራሎች፣ "ይህች ምድር የኛ ናት፣ ከምጽዋ አልፋችሁ አንድ ስንዝር መግባት አትችሉም፤ የመጣችሁበትን ባሕር ጠጥታችሁ እዚያው እለቁ እንጂ ወደ ሀገሬ አትገቡም" የሚል ጥብቅ እና የማያወላውል የሉዓላዊነት ማስጠንቀቂያ ላኩ።
ጣሊያኖች ይህንን የጀግና ማስጠንቀቂያ ንቀው፣ የሣሃጢን ምሽግ ለማጠናከር ተጨማሪ ጦር ይዘው ወደ ፊት ሲገሰግሱ ራስ አሉላ ጥር 18 ቀን 1879 ዓ.ም. በዶጋሊ አሸዋ ላይ ጠበቋቸው።
በታላቅ የጦር ስትራቴጂ እና ወደር በማይገኝለት የሀገር ፍቅር ወኔ 500 የሚጠጉ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቁ የጣሊያን ወታደሮችን ከነአዛዣቸው ከኮሎኔል ዴ ክሪስቶፎሪስ ጋር ሙሉ በሙሉ ደመሰሷቸው።
የዶጋሊው ድል መላውን አውሮፓ ያስደነገጠ፣ የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ህልም ያጨለመ፣ የኢትዮጵያን የማይደፈር ሉዓላዊነት በተግባር ያረጋገጠ እና ራስ አሉላን የቀይ ባሕር ዳርቻ የማይበገር ጠባቂ ያሰኘ ታላቅ ታሪካዊ ኩራት ነው።
የዓድዋው ጀግና፡ የጣልያንን ወረራ በድጋሚ መቅጨት
የራስ አሉላ አባነጋ የሀገር ዘብነት በዶጋሊ ብቻ አላበቃም። ከዓመታት በኋላ የጣሊያን ጦር ዳግም ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ በከፍተኛ ትዕቢት ሲዘምት፣ በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በተደረገው ታላቁ የአድዋ ጦርነት ላይ ራስ አሉላ የዐፄ ምኒልክን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብለው ከነሙሉ ሠራዊታቸው በግንባር ቀደምትነት ተሰለፉ።
የአሉላ የጦር መረጃ እና የስትራቴጂ ብቃት በዓድዋ ጦርነት ላይ የላቀ እና ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
ጣልያኖች የኢትዮጵያን ጦር በድንገት ለማጥቃት ሌሊት የሚያደርጉትን ስውር እንቅስቃሴ የራስ አሉላ ሰላዮች ቀድመው በማወቅ መረጃውን ለዐፄ ምኒልክ አደረሱ።
በዚህም የኢትዮጵያ ጦር ሳይዘናጋ ዝግጁ ሆኖ ጠላትን እንዲጠብቅ አስቻሉ። በጦርነቱ ዕለትም የጣሊያንን የጄኔራል አልበርቶኔን ጦር በመክበብ፣ የጠላትን የማፈግፈጊያ መንገድ በመዝጋት እና በማጥቃት ረገድ የራስ አሉላ ወታደሮች የፈጸሙት ጀግንነት የኢትዮጵያን የመጨረሻ ድል ካረጋገጡት የብረት ምሰሶዎች አንዱ ነበር።
አሉላ ጣልያንን ከባሕር በር ጀምሮ እስከ ዓድዋ ተራሮች ድረስ ዕረፍት የነሱ፣ የሀገር ሉዓላዊነት የቁርጥ ቀን ጠበቃ ነበሩ።
የውስጥ ባንዳዎችን ማጽዳት፡ ሀገርን የማዳን ጽናት
የራስ አሉላ የሀገር ፍቅር ጥልቀት የሚለካው በውጭ ወራሪዎች ላይ በነበራቸው ቆራጥ አቋም ብቻ አልነበረም። የውጭ ጠላት ሀገር ውስጥ ዘልቆ መግባት የሚችለው የውስጥ ከዳተኞች (ባንዳዎች) በር ሲከፍቱለት መሆኑን ጠንቅቀው ያውቁ ነበር።
በመሆኑም፣ በጣሊያን የብር ስጦታ፣ በሥልጣን ጥማት እና በውጭ ኃይሎች የሐሰት ቃል ኪዳን ታውረው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አሳልፈው ለመስጠት የሚሞክሩ የውስጥ ባንዳዎችን እና ከዳተኞችን ያለ ምንም ርህራሄ ተፋልመዋቸዋል።
ለራስ አሉላ ሀገርን መውደድ ማለት የሀገርን ጠላት፣ የውጭም ሆነ የውስጥ፣ በእኩል ጽናት መታገል መሆኑን በተግባር አስተምረዋል።
ለእሳቸው ኢትዮጵያዊነት ከምንም እና ከማንም በላይ የከበረ፣ በብር የማይሸጥ እና በሥልጣን የማይለወጥ ቅዱስ እሴት ነበር።
ጠላትን ፊት ለፊት በሚደረግ ጦርነት ማሸነፍ እንደሚቻለው ሁሉ፣ ከውስጥ ሆነው የሀገርን አንድነት የሚቦረቡሩትን ባንዳዎች ማጽዳት የሀገርን ህልውና ለማስቀጠል ዋነኛው እና የማይታለፈው እርምጃ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል።
ራስ አሉላ አባነጋ መላ ዘመናቸውን የሰሜኑን ድንበር እና የቀይ ባሕርን ዳርቻ በንቃት ሲጠብቁ ያሳለፉ የኢትዮጵያ የነጻነት ተምሳሌት ናቸው።
ከጉንደት እና ጉራዕ የግብፅ ጦርነት አንስቶ እስከ ዶጋሊ፣ ከአይለት አሸዋ እስከ ዓድዋ ተራሮች ድረስ፣ የኢትዮጵያ አፈር በውጭ ወራሪዎች እንዳይረገጥ የከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት እና ያሳዩት ቆራጥ ወታደራዊ አመራር፣ ዛሬም ድረስ በትውልዱ ልብ ውስጥ በአኩሪ ታሪክነት ይኖራል።
የእሳቸው ታሪክ የሩቅ ዘመን ተረት ሳይሆን፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያ የብሔራዊ ስነ-ልቦናዋን የምትገነባበት፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን በንቃት የምትቃኝበት፣ የውስጥ ባንዳዎችን አደጋ የምትገነዘብበት እና ታሪካዊ የባሕር በር ጥያቄዋን በጽናት የምታስጠብቅበት የዘላለም የነጻነት ትምህርት ቤት ነው።
ራስ አሉላ አባነጋ የቀይ ባሕር ዳርቻው ነበልባል፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የማይደፈር ጠበቃ እና እውነተኛ የሀገር ፍቅር ትርጉም ምን እንደሆነ በደማቸው ጽፈው ያለፉ የማይሞቱ ጀግና ናቸው!
የክብር ስማቸው በታሪክ ገጾች ላይ ለዘላለም ሲያበራ ይኖራል!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: