በአንድ ሀገር የኅልውና ታሪክ ውስጥ የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብን ሰላምና የድንበር ደኅንነትን ለማስከበር ከፊት ተሰልፎ መስዋዕትነት የሚከፍል ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት መገንባት እጅግ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት በረዥም ታሪኩ በርካታ ውስብስብ እና ፈታኝ ሁኔታዎችን ቢያልፍም፣ በሚያሳየው ወደር አልባ ፅናት እና በፅኑ የሀገር ፍቅር መንፈስ የሀገርን ሰላምና አንድነት በማስጠበቅ ረገድ የማይናወጥ የወቅቱ የፅናት ምልክት ሆኖ ቀጥሏል።
ሠራዊቱ የሀገርን ደኅንነት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ከሚቃጡ አደጋዎች የመጠበቅ ዋነኛ ግዴታውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።
በተለያዩ ጊዜያት የሀገርን ሰላም ለማናጋት፣ የሕዝቦችን አብሮ መኖር ለማደፍረስ እና ሀገርን ለማፍረስ የሚሸረቡ የባንዳዎችና የጠላቶች ሴራዎችን በከፍተኛ ወታደራዊ ዲስፕሊን፣ በስልታዊ አመራር እና በጀግንነት እያከሸፈ ነው።
ንጹሃን ዜጎች ከጥቃት እንዲጠበቁ እና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ውድ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት የሕዝብን ደኅንነት በተጨባጭ እያረጋገጠ ይገኛል።
ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የብሔር፣ የሃይማኖት እና የቋንቋ ልዩነቶች ሳይበግሩት ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ ዓላማ ስር ያሰባሰበ እውነተኛ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ ሆኗል።
ይህ የሠራዊቱ ጥንካሬ የሚመነጨው ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ከተጣመሩ አባላቱ የጋራ ፍቅር እና ለአንዲት ሀገር ከቆመ ፅኑ መርህ መሆኑ ሲገለጽ፣ እያንዳንዱ አባል የግል ማንነቱን ለሀገር ሉዓላዊነት አሳልፎ በመስጠት ሕዝቦች የአብሮነት አርዓያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ሀገራችን በታሪኳ ከተጋፈጠቻቸው ዘመናዊ ፈተናዎች፣ የጂኦፖለቲካ ጫናዎች እና የውስጥ አለመረጋጋቶች አንጻር የመከላከያ ሠራዊቱ የተጫወተው ሀገራዊ ሚና እጅግ የጎላ ነው።
ሠራዊታችን ከቀላል ወታደራዊ ግዴታ ባለፈ የሀገር የጀርባ አጥንት፣ የሰላም ዘበኛ እና የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ማህተም በመሆን የሚያስመዘግበው አንፀባራቂ ገድል፣ በታሪክ ማህደር ውስጥ ሁልጊዜ በክብር ሲወደስ የሚኖር መሆኑ ተብራርቷል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: