የኢትዮጵያን የማምረቻ ዘርፍ ታሪክ በአዲስ መልክ እየቀየረ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሽግግር፣ ኢትዮጵያን ከባዶ ሼዶች ወደ ግዙፍ የነፃ ንግድ ቀጠናዎች እና የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ባለቤትነት እያሳደጋት ነው።
ከለውጡ በፊት የሎጂስቲክስና የገበያ ትስስርን ታሳቢ ሳያደርጉ በፖለቲካዊ ውሳኔና በከፍተኛ የውጭ ብድር ተገንብተው የነበሩት ፓርኮች፣ አሁን ላይ አዲሱን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተከትለው ተጨባጭ ሀገራዊ ለውጥ እያመጡ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ አዲሱ አቅጣጫ ብክነትን በማስቆም ከቁጥር ይልቅ ወደ ጥራት ያነጣጠረ ነው።
የግንባታ ወጪን በሀገር ውስጥ ተቋራጮች በግማሽ በመቀነስና የግሉ ዘርፍ የራሱን ፓርኮች እንዲገነባ በማበረታታት በተወሰደው እርምጃም ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል።
በዚህም መሰረት በፓርኮች ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች ቁጥር ከ36 ወደ 300 ሲያድግ፣ የሼድ አጠቃቀም ከ45 በመቶ ወደ 88 በመቶ ከፍ ብሏል።
ከተጠቃሚዎቹ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሆናቸው ደግሞ የኢኮኖሚው ሉዓላዊነት ወደ ዜጎች እየተመለሰ መሆኑን ያሳያል።
ይህ አሀዛዊ ስኬት የመጣው "ኢትዮጵያ ታምርት" በተሰኘው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በተተገበረው ስትራቴጂ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ለልብስ ስፌት ዚፕ እና ቁልፍ ሳይቀር ከውጭ ይገባ የነበረውን አሰራር በመቀየር ሰፊ የግብአት ትስስር ተፈጥሯል።
ከተዘጉት ውስጥ ከ800 በላይ ፋብሪካዎች ዳግም ወደ ስራ የገቡ ሲሆን፣ የምግብ ዘይት፣ ሴራሚክና መስታወትን ጨምሮ 96 ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬ ፍሰትን በከፍተኛ ደረጃ መግታት ተችሏል።
የኢትዮጵያ አዲሱ ራዕይ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና የነፃ ንግድ ቀጠናዎች ማሳደግ መሆኑ የተመላከተ ሲሆን፣ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በተቋቋመ በጥቂት ወራት ውስጥ ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግብይት ማስተናገዱ ነው።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ ንፁህ ኢነርጂ፣ ግዙፍ የአየር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ እና በቴክኖሎጂ የታነፀ ወጣት የሰው ኃይል ቁልፍ ምሰሶዎች ሆነዋል።
ሆኖም ይህ ራዕይ በተጨባጭ መሬት ሊነካ የሚችለው የፋይናንስ ዘርፉ የካፒታል ምደባ ስርዓቱን ሲያስተካክል ነው።
ባንኮች ውድ የውጭ ምንዛሬን ተጠቅመው አስር የቅንጦት መኪናዎችን ከሚያስገቡ ነጋዴዎች ይልቅ፣ ያንን ካፒታል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ለሚታደግ ምርት እና ለእሴት ጭማሪ ፋይናንስ ማድረግ ሲጀምሩ የኢትዮጵያ የማምረቻ ኢንዱስትሪ በእርግጥም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችል አሳይቷል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: