Search

በጋምቤላ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ልማት የማሸጋገር ታሪካዊ ጥሪ በምክር ቤቱ ጉባኤ ተስተጋባ

ሰኞ ነሐሴ 11, 2018 54

በጋምቤላ ክልል የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረውና ወደ ላቀ የልማት ምዕራፍ እንዲሸጋገር ለማስቻል፣ ከምክር ቤት አባላትና ከመላው ዜጋ ትልቅ ሀላፊነት እንደሚጠበቅ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ መሰረት ማቲዎስ አሳሰቡ።

አፈጉባኤዋ ይህንን ጥሪ ያስተላለፉት ዛሬ በይፋ በተጀመረው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ምክር ቤቱ የህዝቡን የልማት ፍላጎትና እውነተኛ ድምፅ በመወከል የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የገለፁት ወይዘሮ መሰረት፣ በተጠናቀቀው የበጀት አመት በመልካም አስተዳደር የታዩ ክፍተቶችን በማረም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አብራርተዋል።

ይህም የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ ወሳኝ መሰረት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚኖረው የምክር ቤቱ የጉባኤ ቆይታ የክልሉ አስፈፃሚ አካላት፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የዋና ኦዲት መስርያ ቤት የ2018 በጀት ዓመት የአስራ ሁለት ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ይደረግባቸዋል።

በተጨማሪም የክልሉ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ፣ ማስፈፀሚያ በጀት፣ ተጨማሪ የበጀት አዋጅ እንዲሁም ልዩ ልዩ ረቂቅ አዋጆችና ጉዳዮች ለጉባኤው ቀርበው እንደሚፀድቁና የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥባቸው በጉባኤው ላይ ተገልጿል።

በሚፍታህ አብዱልቃድር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: