የክረምቱ ቅዝቃዜ ማብቂያ ሲቃረብ የፀሐይ ብርሃን ምድርን ዳግም ማሞቅ ሲጀምር፣ የኢትዮጵያዊነት ማህበራዊ ትስስር እና የመንፈሳዊነት ህብረ-ቀለም የሆነው የቡሄ (ደብረ ታቦር) በዓል መቃረቢያው እና ዋዜማው ላይ "መጣና በዓመቱ... ኧረ እንደምን ሰነበቱ!" የሚለው የታዳጊዎች ጭፈራ በያካባቢው መታየት ይጀምራል።
በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ በታላቅ ደስታ የሚከበረው "ቡሄ" የብርሃንና የተስፋ ማበሰሪያ ከመሆኑም በላይ፣ ትውልድን ከሀገር ፍቅር እና ከአብሮነት እሴት ጋር የሚያስተሳስር ታላቅ ህዝባዊ ሀብት ነው።
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ብርሃን በደብረ ታቦር ተራራ ላይ መገለጡን በማሰብ "ደብረ ታቦር" ተብሎ የሚከበረው ይህ በዓል፤ "ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት" እንደሚባለው የዝናብና የጨለማው ወቅት ማለፉን፣ የልምላሜና የብርሃን ዘመን መምጣቱን ያበስራል።
የታዳጊዎች የሆያ ሆዬ ጭፈራ፣ በቃጫ አምሮ እና ተገምዶ የሚሰራው የጅራፉ ድምጽ፣ ከእምዬ ጓሮ የሚያውደው የሙልሙሉ ሽታ የቡሄ በዓል የብዙዎቻችን የልጅነት ትዝታ ማህደር ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የተጋመደ ማንነት እና አንድነት እንዳለን በግልጽ ከሚያመለክቱ እሴቶቻችን አንዱ የሆነው "ቡሄ" በአንድ አካባቢ እና ቋንቋ ብቻ የታጠረ አለመሆኑ በግልጽ ይታያል።
ታዳጊዎችና ወጣቶች በየቡድን ሆነው
"ሆያ ሆዬ ሆ
ሆይ የኔ ጌታ፤ ሆ
ጌታ ለጌታ ፤ ሆ
ቡሄ በሉ ፤ ሆ
ልጆች ሁሉ ሆ " ...
እያሉ በዱላ እና በከበሮ የታጀበ ውብ ዜማ በየደጁ ሲያዜሙ፣ እናቶች ደግሞ በኮባ ተጠቅልሎ የተጋገረውን ልዩ መዓዛ ያለው "ሙልሙል" ዳቦ ያድሏቸዋል አልያም ለጨፈሩ ልጆች በጋራ የሚካፈሉት ጥቂት ገንዘብ ከአባቶች ምርቃት ጋር እንካችሁ ይሏቸዋል።
በአማራ ክልል በደብረ ታቦር፣ በሰሜን ወሎ፣ በጎጃም፣ በሸዋ፣ በወሎና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች በደመቀ ሁኔታ የሚከበር ቢሆንም፣ እሴቱ ግን የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት ነው።
የቡሄ በዓል በኦሮሚያ ክልልም የተለያዩ አከባቢዎች በተመሳሳይ "ኡኬ" (Ukee) በመባል ይታወቃል። በዓሉ ምሽት ላይ የሚከበር ሲሆን፣ ልጆቹ ከብቶችን በዜማ ያሞግሳሉ፤ ከበዓሉ ቀደም ብለው ልጆች ጅራፍ በማዘጋጀት ምሽት ላይ ተሰብስበው ጅራፍ ያስጮሃሉ፤ እንዲሁም ዱላ በመያዝ በየመንደሩ እየተዘዋወሩ ባለቤቶቹን በበጎ ስም በመጥራትና ውብ ግጥሞችን በመግጠም ያመሰግናሉ።
ይህ በዓል ልጆች ወዳጅነታቸውንና ጓደኝነታቸውን እንዲያጠናክሩ፣ የአካባቢያቸውንና ሁኔታ እንዲያውቁ፣ እንዲሁም ግጥም በመግጠም የዜማ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።
በዚህን ወቅት ልጆች
"Ukee yaa ukee
Ukee bara kaanii
Kan miilli dagaanii
Ukee bara quufaa
Hindaaqqoo dhudhuufaa..."
እንዲህ እያሉ ያዜማሉ
ልጆች ሙልሙል ዳቦውን እየገመጡ በየሰፈሩ የሚገርፉት የጅራፍ ድምፅ የክረምቱን ጨለማ መገፈፍ የሚያበስር ሲሆን፣ በምሽት የሚለኮሰው ችቦ ደግሞ አካባቢውን በብርሃን ያሸበርቀዋል።
ይህ ከልጅነት ጀምሮ በልባችን የሚታተመው የማካፈል፣ የመተሳሰብ እና የእንግዳ ተቀባይነት ባህል፤ ህፃናት ስለ ሀገራቸው ፍቅር፣ ስለ ወገን ደስታ እና ስለ ህብረት ትልቅ ትምህርት የሚያገኙበት የቀደመ ማህበራዊ መሰረት ነው።
ቡሄ በዜማና በደስታ ብቻ የሚገለፅ ሳይሆን፤ የቤተሰብ ፍቅርን፣ የጎረቤት ትስስርን እና የህብረ-ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ሌላኛው ድልድይ ነው።
የቡሄ በዓል መንፈሳዊ ጥልቀቱን ጠብቆ ከማህበራዊ ትስስር ማጠናከር ባለፈ፣ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች የማይረሳ ትዝታን የሚፈጥር፣ የቱሪዝም ኢኮኖሚን ከፍ የሚያደርግ እና የሀገራችንን በጎ ገጽታ ለዓለም የሚያስተዋውቅ ድንቅ ብሄራዊ ፀጋችን ነው።
የቡሄ በዓል በእናንተ አካባቢ ምን ተብሎ እንደሚጠራ በመልእክት መስጫው ላይ አጋሩን።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: