ኢትዮጵያ በነቃ፣ ሁለገብ እና ስልታዊ የዲፕሎማሲ አካሄድ በቀጣናዊ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በጥንካሬ እያረጋገጠች ትገኛለች።
በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የተመዘገቡት ስኬቶች ብሔራዊ ጥቅምን ከማስከበር ባሻገር ለቀጣናዊ ሰላም እና ለኢኮኖሚያዊ ውህደት መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።
ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ መረጋጋት እና የጋራ እድገት የሚደረገው ጥረት የቀጣናዊ ዲፕሎማሲ ዋና ማዕከል ሆኖ ቀጥሏል።
በተለይም በጎረቤት መንግሥታት መካከል የመሰረተ ልማት ትስስርን በማስፋፋት ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኬንያ፣ ለጅቡቲ እና ለሱዳን እያቀረበ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር መስመር የፈጠረው የትራንስፖርት እና የንግድ ቅብብሎሽ ጠንካራ ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ማረጋገጥ ችሏል።
በተጨማሪም የሚነሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና አሸባሪነትን በጋራ ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና የማይተካ ነው።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ መስዋዕትነት የምትከፍለው እና በሱዳን ያለውን ግጭት በውይይት ለመፍታት የምታደርገው ጥረት፣ "ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ" የሚለውን መርህ በተግባር ያሳየ ነው።
ይህ የዲፕሎማሲ አቋም የአህጉሪቱን ክብር እና ነፃነት የሚያስጠብቅ፣ ውጫዊ ጫናዎችን የሚመክት እና አፍሪካውያን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዲወስኑ የሚያስችል አህጉራዊ ተምሳሌት ሆኗል።
በዓለም አቀፍ ተቋማት እና መድረኮች የኢትዮጵያ ድምፅ እና ተፅዕኖ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ መጥቷል።
ከጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የጂኦ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ክብደት የሚያሳይ ታላቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው።
ይህ አባልነት አማራጭ የልማት ፋይናንስን ለማግኘት እና ከታዳጊ ዓለማት ጋር ሰፋ ያለ የንግድ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ በር የከፈተ ታሪካዊ ክስተት ነው።
ኢትዮጵያ በነቃ የዲፕሎማሲ አካሄዷ ያላትን የጂኦፖለቲካዊ ብልጫ በመጠቀም ያጋጠሟትን ፈተናዎች ወደ ስልታዊ መልካም አጋጣሚዎች እየቀየረች ትገኛለች።
ይህ እያደገ የመጣ ተፅዕኖ ፈጣሪነትም ለነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ እድገት እና ለዓለም አቀፍ ክብሯ ጽኑ መሠረት እየጣለ ይገኛል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: