አንድ ሀገር ታሪኳን፣ ሕዝቧን እና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ ለማቆየት አስተማማኝ እና የሀገር መከታ የሆነ ሠራዊት ያስፈልጋታል።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት የከፈለው ታላቅ ዋጋ የብዙ ጀግኖች ደም፣ ላብ እና መስዋዕትነት ውጤት ነው።
ይህንን ታሪካዊ አደራ በትከሻው ተሸክሞ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሸጋገረው የመከላከያ ሠራዊታችን ከሕዝብ የወጣ፣ ለሕዝብ የሚኖር እና ለኢትዮጵያ ህልውና በአንድ ዓላማ የቆመ ታሪካዊ ተቋም ነው።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ታሪክ ዛሬ የጀመረ ሳይሆን ሥሩ ከጥንታዊ ሥልጣኔያችን ጋር የተሳሰረ ነው።
ጋሻ እና ከጦር ተጠቅሞ ሉዓላዊነትን የመጠበቅ ባህል ያላት ኢትዮጵያ በብዙ ዘመናት ወራሪዎችን በመመከት ክብሯን አስከብራ ኖራለች።
ከዓድዋ አንጸባራቂ ድል እስከ ዘመናዊው የሀገር ጥበቃ ሥርዓት ድረስ፣ ሠራዊቱ የውጭ ወረራን እና የውስጥ ስጋቶችን በመቀልበስ ደማቅ የታሪክ ምዕራፎችን ጽፏል።
ይህ ኃይል ሁልጊዜ የአንድነት ምልክት ሲሆን፣ ከሁሉም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የመጡ ልጆች በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር ተሰልፈው ለእናት ሀገራቸው ይቆማሉ።
ሠራዊታችንን የሚያስተሳስረው ብሔር፣ ሃይማኖት ወይም አካባቢ ሳይሆን ጠንካራ የሀገር ፍቅር እና የሕዝብ አገልግሎት ብቻ ነው።
በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ የዘመኑን የጦርነት ባሕሪ ተረድቶ ራሱን በከፍተኛ ደረጃ አዘምኖ ኢትዮጵየን በሚመጥን ቁመና ላይ ተገኝቷል።
ትናንት በጋሻ እና በጦር ይደረግ የነበረው ተጋድሎ ዛሬ በቴክኖሎጂ፣ በዘመናዊ ትጥቅ፣ በመረጃ አቅም እና በላቀ የአየር ኃይል ብቃት የተደገፈ ሆኗል።
የኢትዮጵያ መከላከያ አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ ለውጥ ጋር በመራመድ የሳይበር ደኅንነት አቅሙን፣ የድሮን ቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን እና የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ዘርፉን እያሳደገ ይገኛል።
ዘመናዊ የመከታተያ ሥርዓቶች፣ እጅግ የላቀ የአየር ኃይል ብቃት፣ ዘመናዊ የመረጃ አሰባሰብ፣ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎች እና የዘመናዊ ሥስልጠና ሥርዓቶች ከአባቶቹ ከወረሰው ጀግንነቱ ላይ ታላቅ እሴት ጨምሮ የሠራዊቱን ብቃት ወደ የላቀ ዘመናዊ ብቃት አሸጋግረውታል።
በተለይም የዘመናዊ ጦርነት መለያ የሆነውን ፍጥነት እና ትክክለኛ መረጃ መሠረት በማድረግ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ የምድር ኃይሎችን ከማገዝ ባለፈ የሀገር ደኅንነትን የማስከበር ዋነኛ ምሰሶ ሆኗል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ በድንበር ጥበቃ ብቻ አይገደብም፡፡ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን መልካም ስም በዓለም አደባባይ አስጠርቷል።
ታሪካዊውን የኮሪያ ዘማቾች የቃኘው ሻለቃ ተጋድሎን ጨምሮ፣ በሩዋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ብሩንዲ፣ ሱዳኖቹ ዳርፉር እና አብዬ እንዲሁም በሶማሊያ ሰላምን ለማስከበር የተሰማሩ የሠራዊታችን አባላት በብቃታቸው፣ በሥነ-ምግባራቸው እና በሰብዓዊ አገልግሎታቸው የዓለምን ክብር አትርፈዋል።
ይህም የመከላከያ ተቋማችን ጥንካሬው በጦርነት አውድማ ብቻ ሳይሆን በሰላም ግንባታም ታላቅ መሆኑን ያረጋግጣል።
ዛሬ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የትናንትን የጀግንነት ታሪክ ጠብቆ፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ አቀናጅቶ እና ለነገዋ የበለጸገች ኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ሆኖ የሚጓዝ ኩሩ ተቋም ነው።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: