ለዘመናት ስፖርት የደስታ፣ የመዝናኛ እና የሕዝቦች ወዳጅነት ማጠናከሪያ ሆኖ ኖሯል።
በዘመናዊው ዓለም ግን ከውድድር ባሻገር የሀገራትን ኢኮኖሚያዊ መዋቅር የሚቀይር፣ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርትን (GDP) የሚያሳድግ እና ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ግዙፍ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ከሆነ ውሎ አድሯል።
ዓለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የዓለም አቀፉ የስፖርት ኢንዱስትሪ ዓመታዊ የገንዘብ እንቅስቃሴ ከሦስት ትሪሊዮን ዶላር በላይ አልፏል።
እንደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ የስፔን ላሊጋ እና ኤን.ቢ.ኤ (NBA) ያሉ ታላላቅ ውድድሮች፣ እንዲሁም የኳታር፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ ስፖርት የመሠረተ ልማት፣ የቱሪዝም እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ መፍጠሪያ ዋነኛ መንገድ ሆኗል።
በኢትዮጵያም መደመርን እንደ ሀገራዊ የዕድገት ዕሳቤ ከተቀበልንበት ጊዜ ጀምሮ፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን መገንባት የሰዎች ሁለንተናዊ ዕድገት እና የኢኮኖሚ ሕዳሴ አካል ተደርጎ ተይዟል።
የመደመር አቅጣጫ የሰውን ልጅ አቅም ከተፈጥሮ እና ከቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት አዲስ ዕሴት መፍጠር ላይ ያተኩራል።
መንግሥት መሠረተ ልማትን ይገነባል፤ የግል ዘርፉ አገልግሎት እና ንግድን ያስፋፋል፤ ወጣቶች እና ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ያገኛሉ። በዚህ ሒደት ስፖርት ከመዝናኛ ባሻገር ሰፊ የኢኮኖሚ ሰንሰለት ይፈጥራል።
በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የሚገነቡ ዘመናዊ ማዘውተሪያዎችም ይህንን አቅም ያሳያሉ። ግንባታቸው በራሱ የሥራ ዕድል ሲፈጥር፣ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ደግሞ የጂም እና የሥልጠና ማዕከላት፣ የስፖርት ቁሳቁስ ንግድ፣ ምግብ እና መጠጥ፣ መጓጓዣ እና የመዝናኛ እንቅስቃሴዎችን ያነቃቃሉ።
በቅርቡ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት የበቁት የቀበና ወንዝ ዙሪያ የመዝናኛ ስፍራዎች እና በኮሪደር ልማት የተሠሩ የብስክሌት እና የእግር ጉዞ መስመሮች፤ የመዝናኛ ተቋማት፣ የወጣቶች ሥራ ዕድል እና የጎብኚዎች ፍሰት ተደምረው አዲስ የከተማ ኢኮኖሚ ምኅዳር ይፈጥራሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ዘመናዊ ማዘውተሪያዎች ኢትዮጵያ አኅጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ለማስተናገድ ያላትን አቅም ያሳድጋሉ። ይህም የውጭ ምንዛሪ ፍሰትን በመጨመር ለስፖርት ቱሪዝም እና ለሀገራዊ ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ይሁን እንጂ ማዘውተሪያዎችን መገንባት ብቻውን በቂ አይደለም። ተቋማቱ በተሟላ አቅም መሥራት፣ በዘላቂነት መመራት እና ከግል ዘርፍ ጋር ተቀናጅተው ኢኮኖሚያዊ ዋጋ ማመንጨት አለባቸው። የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች፣ የግል ኢንቨስትመንት፣ የጎብኚዎች ፍሰት እና የተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ዕሴት ሊለካ ይገባል።
የስፖርት ማዘውተሪያዎች ለስፖርተኞች የልምምድ ቦታ ብቻ አይደሉም፤ ለወጣቶች የሥራ ዕድል፣ ለባለሀብቶች የንግድ መድረክ፣ ለከተሞች የቱሪዝም መስህብ እና ለሀገር ዓለም አቀፍ መገናኛ ናቸው። ስለሆነም የስፖርት ልማትን በሜዳ እና በሜዳሊያ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚያዊ ዕሴቱ መለካት ያስፈልጋል።
የተፈጠረው የሥራ ዕድል፣ የተንቀሳቀሰው ኢንቨስትመንት፣ የጨመረው የቱሪዝም ፍሰት እና በሀገር ውስጥ የተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ዕሴት አብረው ሊታዩ ይገባል።
ለኢትዮጵያ ስፖርት የሚውለው ሀብት የሚገነቡ ማዘውተሪያዎች በትክክል ከተመሩ፣ ስፖርትን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚን፣ ሥራን፣ ቱሪዝምን እና የወጣቶችን ተስፋ በአንድ ላይ ሊያሳድጉ ይችላሉ።
ስለሆነም የስፖርት ኃይል ከመሠረተ ልማት፣ ከግል ዘርፍ፣ ከወጣቶች፣ ከቱሪዝም እና ከሰው ኃይል ጋር ሲቀናጅ፣ የስፖርት ድል እና የኢኮኖሚ ዕድገት ተለያይተው የሚታዩ አይሆኑም፤ በአንድ ሀገራዊ የልማት ጉዞ የሚደመሩ ኃይሎች ይሆናሉ።
በአዲስ የሺዋስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: