የቴክኖሎጂ አብዮት ዓለምን በከፍተኛ ፍጥነት እየቀየረ ባለበት በዚህ ዘመን፣ የከተሞች አሠራር ከዲጂታላይዜሽን ጋር መተሳሰር አማራጭ የሌለው የልማት ምዕራፍ ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ሲሆን፣ ይህንን ፈጣን የከተማ መስፋፋት ተከትሎ የሚመጡ እንደ የትራፊክ መጨናነቅ፣ የአካባቢ ብክለት እና የመሠረተ ልማት ጫናዎችን ለመቋቋም ዘመናዊ እና ዲጂታል አቀራረቦች ወሳኝ ናቸው።
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በስፋት እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የትራንስፖርት መሠረተ ልማትን በማዘመን፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን በማስፋፋት እና የሕዝብ መገልገያዎችን በማሻሻል ለዘመናዊ ከተሞች ግንባታ ጠንካራ መሠረት እየጣሉ ይገኛሉ።
እነዚህ ሰፊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች የትራፊክ መጨናነቅን በ30 በመቶ የመቀነስ፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን የመፍጠር እና በየዓመቱ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርትን (GDP) በ2 በመቶ የማሳደግ ትልቅ ዓላማ ያነገቡ ናቸው።
ከዚህ ባለፈም እንደ ሴንሰሮች፣ ዘመናዊ መብራቶች እና ፈጣን የኢንተርኔት ኔትወርኮች ያሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ለመዘርጋት ምቹ ምኅዳር ይፈጥራሉ።
ስማርት ሲቲ ወይም ዘመናዊ ከተማ ማለት የሕዝብን የኑሮ ጥራት ከፍ ለማድረግ፣ ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እና ሀብትን በአግባቡ ለመቆጣጠር ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በስፋት የሚጠቀም ከተማ ማዕቀፍ ነው።
የዲጂታላይዜሽን እና የስማርት ሲቲ ግንኙነት እጅግ የተቆራኘ በመሆኑ፣ ዲጂታል መድረኮች ሲኖሩ የከተማ መሠረተ ልማቶች በብቃት ይመራሉ።
የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የከተማ ተንቀሳቃሽነትን (mobility) ለማሻሻል፣ የሕዝብ ደኅንነትን ለማረጋገጥ፣ የኃይል አጠቃቀምን ቀልጣፋ ለማድረግ እና የአካባቢ ጥበቃን ዘላቂ ለማድረግ እጅግ አስፈላጊ ናቸው።
የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" የስትራቴጂ ሰነድ በከተሞች ዕድገት ሂደት ውስጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ስማርት ከተሞችን ዕውን ለማድረግ ግልጽ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
በዚህም መሠረት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የ5ኛ ትውልድ (5G) ኔትወርክን በመጠቀም የትራፊክ ፍሰትን ማቀላጠፍ፣ መጨናነቅን አስቀድሞ መተንበይ እና የከተማ ደኅንነትን መጠበቅ ከዋና ዋና ስትራቴጂዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
እንዲሁም የኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ (IoT) ሴንሰሮችን በመዘርጋት የአካባቢ ብክለትን፣ የአየር ጥራትን እና የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን በመረጃ ላይ ተመሥርቶ መከታተል የሚችሉ የከተማ ዳሽቦርዶች እንዲኖሩ ይደረጋል።
ከዚህ በተጨማሪ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ከፍላጎት አስተዳደር ጋር የሚያስተሳስሩ ዘመናዊ የኃይል አውታሮች እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ትኩረት ተሰጥቷል።
የከተማ ፕላን አሠራርን ለማዘመን እና አዳዲስ መዋቅራዊ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ተግባር ከመቀየራቸው በፊት በቨርቹዋል ዓለም ሞክሮ ለማየት የ‘ዲጂታል ትዊንስ’ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም በዕቅዱ ተካትቷል።
ይህንን ሂደት ከዓለም አቀፍ ልምዶች አንጻር ስንመለከተው፣ እንደ ደቡብ ኮሪያ ያሉ ሀገራት ‘ቢግ ዳታ’ በመጠቀም የሕዝብ አውቶቡስ መስመሮችን በማስተካከል የትራፊክ መጨናነቅን መቀነሳቸው ጥሩ ማሳያ ነው።
እንዲሁም ሲንጋፖር ‘ቨርቹዋል ሲንጋፖር’ የተሰኘውን ባለ (3D) ዲጂታል ግልባጭ በመጠቀም የከተማ ፕላን ሥራዎችን በብቃት ማከናወኗ እና ዱባይ የከተማ አስተዳደር አገልግሎቶችን በአንድ ዲጂታል መተግበሪያ ማቀናጀቷ ለዘመናዊ ከተሞች ግንባታ ዲጂታላይዜሽን ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ያሳያል።
የከተማ አስተዳደር አገልግሎቶችን ግልጽ፣ ፈጣን እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ሚና የማይተካ ነው።
"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ያስቀመጣቸው ግቦች ስማርት ከተሞችን እውን በማድረግ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የከተሞችን ኑሮ ምቹ እና ዘመናዊ ለማድረግ ትልቅ መሠረት የሚጥሉ ናቸው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: