በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የምክክር ጉባኤ እንደ ሀገር የገጠሙንን ዘርፈ ብዙ ስብራቶች በመጠገን የሕዝብን አብሮነት እና ዘላቂ ሰላምን የሚያጸና በጎ ጅምር መሆኑን የባሕር ዳር ዙሪያ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
ምክክሩ ለረጅም ዘመናት ሲንከባለሉ የነበሩ የሐሳብ ልዩነቶችን በፍጹም ኢትዮጵያዊነት ስሜት በመደማመጥ እና በመነጋገር እልባት የምናበጅበት መንገድ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ ሀገር ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓትን ጨምሮ ጠቃሚ ዕሴቶች ቢኖሩንም የመደማመጥ፣ የመነጋገር፣ በሐሳብ የበላይነት ያለማመን፣ የእኔ ብቻ ሐሳብ ትክክል ነው የሚሉ የተዛቡ ዕሳቤዎች ለዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች እንደዳረጓቸው ተናግረዋል።
"ግጭት፣ ጦርነት ሰልችቶናል፤ እስከ አሁን የከፈልነው ዋጋ ከበቂ በላይ ነው፤ በሰላም ወጥተን በሰላም መግባት እንፈልጋለን፤ ቀያችንን አርሰን አለስልሰን ጎተራችንን መሙላት፣ ልጆቻችንን ማስተማር፣ ቤተሰባችንን ማስተዳደር እንፈልጋለን። ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት ሊፈቱ ይገባል፤ ለዚህ ደግሞ እየተካሄደ ያለውን ጉባኤ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል" ሲሉ ለኢቲቪ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በዚህ የምክክር ጉባኤም የተነሡ የተለያዩ አጀንዳዎች መግባባት እንደሚደረስባቸው በመግለጽ፣ በተለይም ጉባኤው ዘላቂ ሰላምን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ያስፍናል ብለው በተስፋ እንደሚጠብቁት አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
ጉባኤውንም በሬዲዮ እና በሌሎች የሚዲያ አማራጮች በአንክሮ እየተከታተሉት መሆኑን የተናገሩት አርሶ አደሮቹ፣ በጉባኤው እየተሳተፉ ያሉ ተመካካሪዎችም የእኔ ብቻ ይሁን ከሚል አስተሳሰብ እና አመለካከት ወጥተው የእኛ የሚለውን የጋራ ዕሳቤ በማስቀደም የሕዝብን አደራ ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በተስፋሁን ደስታ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: