Search

ከዲጂታል አሠራር እስከ ዲጂታል ኢኮኖሚ፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የስኬት ጉዞ

ማክሰኞ ነሐሴ 12, 2018 61

በዳታ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በፈጣን የቴክኖሎጂ ግስጋሴ በታጀበው 21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ከተመልካችነት ወደ ዋና ተዋናይነት የተሸጋገረችበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።

ሀገራችን የያዘችውን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ረጅም ርቀት ዓላሚ ስትራቴጂያዊ ራዕይ መሠረት በማድረግ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎቿን በዘመናዊ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች ላይ የመገንባት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ይህ ጉዞ የቴክኖሎጂ ሽግግር ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎችን ዕለታዊ ሕይወት የሚያቀልል፣ አሠራርን የሚያፋጥን እና የኢኮኖሚ ምሰሶዎችን በጽኑ መሠረት ላይ የሚተክል ታላቅ የትራንስፎርሜሽን ማዕበል ነው።

ለዚህ ዘመናዊ እና ፈጣን የዲጂታል ምጥቀት በዋና መሠረትነት እየተጠቀሱ ካሉ የለውጥ አበጋዞች መካከል የዜጎችን ሁለንተናዊ ማንነት በዲጂታል መንገድ ማረጋገጥ ያስቻለው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

ፋይዳ ግልጽነት ያለው እና ደኅንነቱ የተጠበቀ አሠራርን በመፍጠር፣ የመንግሥት እና የግል ተቋማት አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ እና ያለ እንግልት ለዜጎች ተደራሽ እንዲሆኑ አድርጓል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በፋይናንስ ዘርፉ የታየው እና የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች እመርታ፣ ያለ ጥሬ ገንዘብ የሚፈጸሙ የገንዘብ ዝውውሮችን በማስፋፋት ዘመናዊ እና የተቀናጀ የዲጂታል ኢኮኖሚ መሠረት ጥሏል።

የወደፊቷን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ግንባር ቀደም ለማድረግ ደግሞ የሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተበሰረው 5 ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ፣ ወጣቶችን በሶፍትዌር ልማት፣ በዳታ ሳይንስ እና በዲጂታል ክህሎቶች በማነጽ ለነገው የቴክኖሎጂ ዓለም ብቁ እና ተወዳዳሪ የፈጠራ ባለቤቶች እያደረገ ይገኛል።

እንደ መሶብ ያሉ የተቀናጁ የኦንላይን መንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ፕላትፎርሞች መዘርጋታቸው ደግሞ፣ ዜጎች ከየትኛውም ቦታ ሆነው በኢንተርኔት አማካይነት አገልግሎቶችን በፍጥነት እና በቅልጥፍና እንዲያገኙ በማድረግ አስተዳደራዊ እንግልትን በአመዛኙ አስቀርተዋል።

የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ከማስፋፋት ጀምሮ እስከ ፖሊሲ ማሻሻያዎች እና የክህሎት ግንባታዎች ተቀናጅተው እየተከናወኑበት ያለው ይህ ሁለንተናዊ የትራንስፎርሜሽን ጉዞ፣ ኢትዮጵያን 2030 የአፍሪካ የቴክኖሎጂ፣ የኢኖቬሽን እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባር ቀደም ማዕከል ለማድረግ የተያዘው ትልቅ ሀገራዊ ሕልም እውን እንዲሆን እያስቻለ ይገኛል።

በሔዋን ጌታቸው

 

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: