Search

የባህር በር የፍትሃዊነት፣ የታሪክ እና የቀጣናዊ እድገት መሠረት

ሰኞ ነሐሴ 11, 2018 75

የቀይ ባህር ጉዳይ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ስልጣኔ፣ ሀገረ-መንግሥት ስሪት፣ ደህንነት እና ምጣኔ ሀብታዊ ራዕይ በእጅጉ የተቆራኘበት፤ የትውልዱ ህልውናና የሉአላዊነት ማረጋገጫ ጥያቄ በመሆኑ መንግሥት ጥያቄውን እውን ለማድረግ ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

 ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አቅራቢያ የምትገኝ የታሪካዊ የባህር በር ባለቤት የነበረች ቢሆንም፣ በታሪክ አጋጣሚ የቀጣናው ታዛቢና የጂኦ-ፖለቲካ እስረኛ እንድትሆን ተደርጋለች።

ይሁን እንጂ የሕዝቧ ቁጥር በፍጥነት ማደጉንና የቀጣናውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ፣ የባህር በር ማግኘት የቅንጦት ፍላጎት ወይም የፖለቲካ አጀንዳ ሳይሆን የታሪክ፣ የሕግ፣ የፍትሃዊነት እና የመጭው ትውልድ የመኖርና ያለመኖር ሁለንተናዊ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ በአፅንዖት ገልፀዋል።

ይህንን የሀገርና ሕዝብ ጥያቄ እውን ለማድረግ መንግሥት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላማዊ መንገድ፣ በንግድ፣ በሎጂስቲክስና በባህር ትስስር አብሮ ለማደግና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ውይይት ለማድረግ ጥሪ ማቅረቡን የቀጠለ ሲሆን፣ ጥያቄው የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት የመጋፋት ሳይሆን፣ የጋራ የንግድ ትስስርን በማጠናከር የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና የሰላምና የብልጽግና ማዕከል የማድረግ ራዕይ ያለው ነው።

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆኗ ለራሷ የኢኮኖሚ ዕድገት ብቻ ሳይሆን፣ ጠንካራ የባህር ኃይልና የወደብ መዋቅር በመገንባት በቀይ ባህር አካባቢ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት ለመፍጠር የጎላ ሚና ይኖረዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚገነቡ የወደብ መሠረተ ልማቶች፣ የነጻ ንግድ ቀጣናዎችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ በመሆናቸው፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥት ለብሔራዊ ጥቅም የያዘውን ጥንካሬና የዲፕሎማሲ ጥረት ድጋፉን በመስጠት ከጎኑ ተሰልፎ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ዕቃዎችን ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሞጆና አዲስ አበባ ደረቅ ወደቦች ለማጓጓዝ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚወጣ ሲሆን፣ ዕቃዎች በወቅቱ ከወደብ ሳይነሱ ሲቀሩ በየቀኑ የሚታሰበው የኮንቴይነር መቆያ ቅጣትና የመጋዘን ኪራይ ወጪውን ይበልጥ ያንረዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ያነሳችውን የባህር በር የባለቤትነት ጥያቄ ስታሳካ ግን ይህ ሁሉ ወጪ ቀርቶ ገንዘቡ ለሌሎች የልማት ሥራዎች የሚውል ከመሆኑም በላይ፣ በባህር ላይ የሉዓላዊነት ክብርን ለማስከበርና የንግድ መርከቦቿን ከደህንነት ስጋት ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ የባህር ኃይል አቅም ለመገንባት ያስችላታል።

ባለፈው ታሪክ የባህር በር በማጣቷ በርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ያጣችው ኢትዮጵያ፣ የባህር በር ባለቤት መሆኗ የወደብ ኪራይ ወጪን በማስቀረትና ቀልጣፋ የንግድ ሥርዓት በመዘርጋት የሀገሪቱን ብልፅግና እንደሚያፋጥነው ተጠቅሷል።

በመሆኑም ይህንን ወሳኝ ሀገራዊ ግብ ማሳካት ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥር፣ በወታደራዊ አቅም እና በዲፕሎማሲ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተወዳዳሪነት እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ይሆናል።

 

በኢንቲሃድ አብራር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: