Search

የዓለም የሰብዓዊነት ቀን

Aug 19, 2025

በየዓመቱ ነሐሴ 13 የሚከበረው የዓለም የሰብዓዊነት እርዳታ ቀን፣ ሌሎችን በመርዳት ሕይወታቸውን ያጡትን ጨምሮ ለሰብዓዊ አገልግሎት ሰራተኞች ክብር ለመስጠት የሚከበር ዓለም አቀፍ ቀን ነው።

አላማውም ስለ ሰብዓዊ እርዳታ እና ስለ ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊነት ግንዛቤን ማሳደግ ነው።

ቀኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፣ ነሐሴ 13 የዓለም የሰብዓዊነት ቀን ተብሎ ተሰይሟል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በችግር ውስጥ ላሉ ማህበረሰቦች ተስፋ እና እፎይታ የሚያመጡ ድጋፎችን በማድረግ፣ ርህራሄ እና ክበር በማሳየት ዕለቱን በሰብዓዊነት ስሜት ያከብራል።

ዛሬ በመላው አፍሪካ እና በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ረሃብ፣ መፈናቀል እና ግጭት ሲገጥማቸው፤ የደጋግ ሰዎች ልግስናን እና የሰብዓዊ መብት አገልግሎት ሰራተኞችን በጎ ተግባር ማየት ተስፋን ይሰጣል።

በተለይ በአፍሪካ የመስጠት እና የመረዳዳት መንፈስ ያላቸው ባሕላዊ ወጎች በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሥር የሰደዱ መሆናቸውንም ያስታውሰናል።

ሰብዓዊነት በሃብት እና በእድገት ብቻ ሳይሆን በመተሳሰብ እና በጋራ ኃላፊነት የሚገነባ መሆኑንም እሙን ነው።

በአፍሪካ የሚኖሩ ሕዝቦች ለዘመናት ባሳለፉት ደግነት እና መደጋገፍ በተግባር የሰውን ልጅ ኃይል በምሳሌነት አሳይተዋል።

ይህ ዕለትም ታዲያ መተባበር እና አብሮ መኖር ባሕሉ ለሆነ ሕዝብ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የተሰጠ ዓለም አቀፍ ቀን ነው።

በሴራን ታደሰ