Search

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን አስጀመሩ

ማክሰኞ ነሐሴ 13, 2017 92

የሚኤሶ ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
የሚኤሶ - ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ሁለት ክልሎችን እና የድሬዳዋ ከተማን እንደሚያስተሳስር የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሎች መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብር የማጎልበት ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ከወደብ ወደ ማዕከላዊ የሀገራችን ክፍል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢ እንዲሆኑና አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖረን ይፈለጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬ የምንጀምረው የፍጥነት መንገድ እነዚህን ሁለት ዓላማዎች የሚያሳካ ነው ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ መንገድ የሚጀመረው ብዙ ባህል በተቀየረበት ጊዜ መሆኑን በመጠቆም፤ መሠረት ድንጋይ አስቀምጦ መጥፋት፣ ጀምሮ መተው፣ ከጥራት በታች ሠርቶ መመረቅና አዘግይቶ የሐገር ሀብት ማባከን ፈጽሞ እንደማይፈቀድም አሳስበዋል፡፡
በቀጣይም የኢትዮጵያን ማንሠራራት የሚያበስሩ አያሌ ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክቶችን እንደሚሰሩና የተጀመሩትም በፍጥነትና ጥራት እንደሚጠናቀቁ አረጋግጠዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሮጀክቱን በጀት ለሸፈነው የዓለም ባንክ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የመንገድ ግንባታው ከዓለም ባንክ በተገኘ የ62 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የሚገነባ ሲሆን፣ ሚኤሶ ቢኬ የ 73 ኪ.ሜ ግንባታ በመጀመርያ ምዕራፍ ቢኬ ድሬዳዋ የ71 ነጥብ 4 ኪ.ሜ ግንባታ ደግሞ በሁለተኛ ምዕራፍ ይከናወናል፡፡
በ4 ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው ይህ ፕሮጀክት፤ ከዚህ ቀደም ከ 5 ሰዓት በላይ ይወስድ የነበረውን የመንገድ ጉዞ ከ1 ሰዓት 30 በታች እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡
በአሸናፊ እንዳለ