በኢትዮጵያ የባህል ካዝና ውስጥ እጅግ ደማቅ ከሆኑት እና ጥልቅ ማኅበራዊ ትርጉም ካላቸው በዓላት መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ የሚከበሩት አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛሉ።
ከነሐሴ አጋማሽ አንስቶ እስከ አዲስ ዓመት ዋዜማ ድረስ የሚዘልቁት እነዚህ በዓላት ከጭፈራ እና ከጨዋታ ባለፈ የሴቶች የነፃነት አዋጅ መድረኮች ናቸው።
የእነዚህ በዓላት መነሻ የጾመ ፍልሰታ ማብቃት እና የድንግል ማርያም እርገት ይሁን እንጂ፤ ማኅበረሰቡ ለዘመናት ያካበታቸውን ባህላዊ እሴቶች አዋህደው የያዙ ናቸው።
በትግራይ "አሸንዳ"፣ በላስታ ላሊበላ "አሸንድዬ"፣ በዋግ ኽምራ "ሻደይ"፣ እንዲሁም በራያ "ሶለል" በመባል የሚታወቁት እነዚህ ክብረ በዓላት ስያሜያቸው ይለያይ እንጂ መንፈሳቸው አንድ ነው።
ባህላዊው ማኅበረሰባችን በአብዛኛው አባታዊ ሥርዓት የሰፈነበት ቢሆንም እነዚህ በዓላት ግን ይህንን ማኅበራዊ ልማድ የሚሠብሩባቸው የተለዩ አጋጣሚዎች ናቸው።
ልጃገረዶች ከነሐሴ አጋማሽ እስከ አዲስ ዓመት ባለው ጊዜ ከቤት ውስጥም ሆነ ከእርሻ ሥራ ሙሉ በሙሉ ነፃ ይሆናሉ።
ይህ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያዜሙበት፣ የማኅበረሰቡን ጠንካራ ጎን የሚያሞግሱበት እና ቅር ያሰኛቸውን ነገር በድፍረት የሚተቹበት የነፃነት አደባባያቸው ነው፡፡
በእነዚህ በዓላት ላይ የሀብታም ወይም የድሃ ልጅ የሚል የኑሮ ደረጃ ልዩነት አይንፀባረቅም። ሁሉም ልጃገረዶች አረንጓዴ የቄጠማ ቅጠላቸውን ወገባቸው ላይ አስረው፣ በሀበሻ ቀሚስ ተውበው በአንድነት ይጫወታሉ።
ከዚህም ባለፈ በዜማዎቻቸው ውስጥ በሚያስተላልፉት የሰላም እና የፍቅር መልዕክት፣ በተጣሉ ቤተሰቦች እና ጎረቤቶች መካከል እርቅ የሚያወርዱበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑ ክብረ በዓላቱን ልዩ ያደርጋቸዋል።
እነዚህ በዓላት የትውፊት ትምህርት ቤቶች ጭምር ናቸው። ታዳጊዎች ከታላላቆቻቸው የባህል ዘፈኖችን እና አለባበስን በተግባር ይማራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሴቶች በተፈጥሮ ውበታቸው እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ እንዲኮሩ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የራስ መተማመን እንዲገነቡ ያስችላቸዋል።
በተጨማሪም ወጣቶች ለወደፊት የትዳር ሕይወታቸው አጋር የሚመርጡባቸው ጤናማ መድረኮች ናቸው።
ዘመናዊው ዓለም ስለ ሴቶች መብት እና እኩልነት መከራከር ከመጀመሩ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት፣ ኢትዮጵያውያን ለሴት ልጆቻቸው ይህንን የነፃነት እና የክብር አደባባይ መፍጠራቸው የባህሉን የረቀቀ እሴት በግልፅ ያሳያል።
እነዚህ ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክሩ፣ የሰላም እና የፍቅር ተምሳሌት የሆኑ ትልልቅ ባህላዊ እሴቶች ናቸው።
የሴቶች የነፃነት እና የደስታ በዓል የሆኑት እነዚህ ትውፊቶች የኢትዮጵያ የቱሪዝም እና የባህል ዲፕሎማሲ ዋነኛ ምሰሶዎች ሆነው ይቀጥላሉ።
በሲሳይ ደበበ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: