በወሎ ወረባቦ ወረዳ ከቢስቲማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ጫሊ፣ ከቦታዋ ስም በላይ ስሟ ጎልቶና ገዝፎ በሀገራችን በስፋት እንዲነሳ ያደረጉት ስመ ገናናው የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ማዲህ ሸህ ሰይድ ኢብራሂም ናቸው።
ማዲሁ ሸህ መሐመድ አወል በግጥማቸው "ስሙ የተጠራው ሰው ቢኖርበት ነው" ብለው እንደገለጹት ሁሉ፤ የጫሊ ምድር በየትኛውም ስፍራ በቱባነቱ እንዲታወቅ ያደረጉት የመንዙማው ባለቅኔ ሸህ ሰይድ ኢብራሂም (ሸህ ጫሊ) ናቸው።
በ1870ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከአባታቸው ሸህ ኢብራሂም ያሲን እና ከእናታቸው ወ/ሮ ዘቡራ ሙሐመድ ተወልደው በራስ ወሌ ቤት ከእቴጌ መነን ጋር ያደጉት እኚህ ታላቅ ሊቅ፤ ፈጣን አእምሮ፣ ከፍተኛ የግጥምና የዜማ ችሎታ የነበራቸው ከመሆኑም በላይ ከአካባቢው ገዥዎችና ከጣሊያን ወራሪዎች ጋር ያደረጉት ትግል፣ እንዲሁም በርካታ የአረብኛና የአጅ ጽሑፎቻቸው ለሀገር ትልቅ አሻራ ጥለው አልፈዋል።
በኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክ ውስጥ የዘመናዊ ነሺዳ ቅልቅል የሌለበትን፣ አልተቀየጠም የሚባለውንና የራሱ ልዩ ቅርጽ ያለው የወሎ ቱባ መንዙማን በጥበብ ቀምረው ለአሁኑ ትውልድ ያቆዩት እኚሁ ባለቅኔ እንደሆኑ ይነገራል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን በይዘትም ሆነ በቋንቋ ልቀት እንደ እርሳቸው መንዙማን የቀመረ እንደሌለ የሚነገርላቸው ሸህ ሰይድ ኢብራሂም የታሪክ ፀሐፊው ከድር ታጁ እንደገለጹት ለክታብ ወገበ-ቀላል የነበሩ የታላቅ ድርሰት "ጋን" ነበሩ።ይላቸዋል፡፡
ከ120 በላይ የግጥም መድብሎቻቸው መካከል በተገኙት 16 መድብሎችና 49 ጥልቅ ስንኞች ላይ ስለ ሀገር አጥብቀው ተጨንቀዋል።
በተለይም “ሚምያ” በመባል የሚታወቀው መድብላቸው በሀገር ላይ የወደቁ የዝናብ እጥረቶችን፣ ድርቅን፣ የእርስ-በርስ ጦርነቶችንና ዳግማዊ የፋሽስት ወረራን በመቃወም ለሀገር ነጻነት፣ ፍትሕና ሰላም በተደረጉ ውጤታማ ዱዓዎችና እርግማኖች የተሞላ ሲሆን፤ ይህም ከመንፈሳቸው ጋር የተጣባውን ጥልቅ ሀገር ወዳድነት ያሳያል።
ከዚህም በላይ ነጥብ የሌላቸውን የአረብኛ ፊደላት ብቻ በመጠቀም “ሙህመል” በተባለ ረቂቅ የአጻጻፍ ስልት የጻፉት ኪታባቸው በግብፅ ሙዚየም ውስጥ የታላቅ ቅርስነት ክብር አግኝቶ ለዓለም ሕዝብ መጎብኛና የታሪክ ማጣቀሻ ሆኖ ይገኛል።
በጫሊ ምድር የተዘራው ይህ የመንፈሳዊነት፣ የጥበብና የሀገር ፍቅር አሻራ ዛሬም ድረስ የሀገራችን ኩራትና የትውልዶች መማሪያ ሆኖ ይኖራል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: