Search

ጉባኤው ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት ሐሳብ እንድናዋጣ ዕድል ፈጥሮልናል፦ ተመካካሪዎች

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 85

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ሁላችንም ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት ሐሳብ እንድናዋጣ ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ።

አስተያየታቸውን ከሰጡ ተመካካሪዎች መካከል ወጣት መርቀኒያ አሊ፣ ጉባኤው እጅግ ስኬታማ፣ አሳታፊ እና እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት የታየበት መሆኑን ተናግራለች።

የምክክር ጉባኤው ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሐሳብ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ጠቁማ፣ የምክክር ሒደቱ በመደማመጥ ለሀገር ግንባታ ሒደቱ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የበሰሉ ሐሳቦች የመነጩበት ትልቅ ዕድል ነው ብላለች።

መሰል ሀገራዊ የምክክር ሒደት ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል ከተደረገ የበለጸገች እና ታላቅ ሀገር ለመገንባት ጥሩ መደላድል እንደሚፈጥርም ነው የገለጸችው።

ይህ ታሪካዊ ሀገራዊ የምክክር ሒደት እስካሁን ለቆዩት ችግሮች የጋራ መፍትሔ ከመስጠት ባለፈ ቀጣዩ ትውልድ ምክክርን ባሕል እንዲያደርግ ጠንካራ መሠረት ጥሎ እንደሚያልፍ ተናግራለች።

ሌላኛው ተመካካሪ ተረፈ ተከራይ በበኩሉ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት ሐሳብ እንድናዋጣ ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ ገልጸዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ቀደም ሲል በሀገሪቱ ለአለመግባባት መንስኤ የነበሩ ጉዳዮችን በጥልቀት ለመመርመር ዕድል የሰጠ ታሪካዊ ጉባኤ ነው ብለዋል።

የምክክር ሒደቱ እኩል ሐሳብ የመስጠት ዕድል የተረጋገጠበትና ፍጹም አሳታፊ እንደነበርም ተናግረዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ሀገርን ወደፊት የሚያራምዱና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ግብዓት የሚሆኑ በሳል ሐሳቦች የተንሸራሸሩበት መሆኑን አብራርተዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው መደማመጥ ላይ የተመሠረተ የሐሳብ መዋጮ የተስተናገደበት በመሆኑ ለሀገር ለዘላቂ ሰላምና አንድነት መጠናከር መሠረት የሚጥል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ ተመካካሪ ወይዘሮ ሐሊማ ሰይድ ናቸው።

ጉባኤው ተመካካሪዎች የአንዱን ችግር እንደራሳቸው እንዲመለከቱ ዕድል በመፍጠር ለጋራ ችግሮች የጋራ የመፍትሔ ሐሳቦች የተመላከቱበት ጉባኤ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣና የጋራ መግባባትን የሚያጎለብት መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

                

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: