Search

የከተሞቻችን አዲስ ንጋት፡ ከመደብ ጠላትነት ትርክት ወደ የተቀናጀ የልማት ማዕከልነት

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 87

የኢትዮጵያን የከተሞች ዕድገት ታሪክ ስንመረምር ዛሬ እየመጣ ያለው ለውጥ የቅርፅ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ የሆነ የፍልስፍና እና የሥርዓት ሽግግር መሆኑን እንረዳለን።

ለዘመናት የኢትዮጵያ ከተሞች በተለይም ባለፉት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አቅጣጫዎች ውስጥ እጅግ የተዛባ ዕይታ ሰለባ ሆነው ቆይተዋል።

አብዮታዊ ዴሞክራሲ የገጠሩን አርሶ አደር ብቻ የልማቱ እና የፖለቲካው ዋልታ አድርጎ በማሰብ ከተሞችን እና የከተማ ነዋሪዎችን በተለይም ምሁራኑን፣ ነጋዴውን እና ባለሀብቱን እንደ መደብ ጠላት እና የፖለቲካ ሥጋት ይመለከታቸው ነበር።

ይህ ጠባብ እና አግላይ ፖለቲካዊ ትርክት በከተሞች ላይ ከፍተኛ የሆነ የመዋቅር እና የበጀት መድልዎ ፈጥሯል። በዚህ ምክንያት መሠረተ ልማት እንዳያድግ፣ ነዋሪዎቻቸውም በጥርጣሬ እንዲታዩ እና ከተሞች የልማት ማዕከል ከመሆን ይልቅ የፖለቲካ ቁጥጥር ጣቢያዎች ብቻ ሆነው እንዲቀሩ አድርጎ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የመደመር መንግሥት ይህንን አጥፊ የመደብ ትግል ትርክት በመስበር ከተሞችን የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ፣ የፈጠራ እና የዜግነት ባህል ግንባታ ዋና ሞተሮች አድርጎ በአዲስ ዕይታ ስሏቸዋል።

በመደመር ፍልስፍና ከተሞች የፖለቲካ ሥጋት ሳይሆኑ ልዩ ልዩ ቋንቋ፣ ሃይማኖት እና ባህል ያላቸው ዜጎች በጋራ እና በሰላም የሚኖሩባቸው የብልፅግና እና የኅብረ ብሔራዊነት ምሰሶዎች ናቸው።

ይህ አዲስ ዕይታ በኢትዮጵያ ከተሞች ላይ እጅግ ተጨባጭ እና ተግባራዊ የሆኑ መዋቅራዊ ለውጦችን እያመጣ ይገኛል።

በተለይም መዲናችን አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ዓለምን ያስደነቀ እና ፈጣን ለውጥ እያመጣች ያለችው በዚህ የመደመር መንግሥት ዕይታ መሠረት ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስትራቴጂ መንገዶች ከተሠሩ በኋላ ለውኃ እና መብራት ቱቦዎች የሚቆፈሩበትን አሮጌ አሠራር በማስቀረት ሁሉም መሠረተ ልማቶች በተቀናጀ መንገድ እንዲዘረጉ አድርጓል።

ከኮንክሪት ግንባታ ይልቅ ለሰው ልጅ ክብር ቅድሚያ የሚሰጡ ሰፊ የእግር መንገዶች፣ የብስክሌት መስመሮች፣ የሕዝብ መናፈሻዎች እና የምሽት ኢኮኖሚን የሚያነቃቁ ዘመናዊ መብራቶች የከተማዋን ገፅታ ሙሉ ለሙሉ እየቀየሩት ነው።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የተከናወኑት እንደ ካዛንቺስ፣ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ እና ቦሌ የመሳሰሉ የኮሪደር ልማቶች ተጠናቅቀው ከተማዋን ለኑሮ ምቹ እና ለንግድ ማራኪ አድርገዋታል።

ቀደም ሲል ለቆሻሻ መጣያነት ያገለግሉ የነበሩ ቦታዎች በወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች አማካይነት ለምተው ወንዞቹ የከተማዋ እስትንፋስ እየሆኑ ናቸው።

እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ እና የዓድዋ ድል መታሰቢያን የመሳሰሉ ግዙፍ ስፍራዎች የዚህ ሰው-ተኮር ልማት ተጨባጭ ማሳያዎች ሆነው የዓለም አቀፍ ተቋማትን አድናቆት ጭምር እያተረፉ ይገኛሉ።

ይህ የተቀናጀው መሰረተ ልማት ከተሞችን ጽዱ እና ለጤና ተስማሚ ለማድረግ የሚያስችሉ የፍሳሽ አገልግሎትን በዘመናዊ መንገድ የተሠራለት ነው።

ይህ የተሳካ እና ከተሞችን የክትመት ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ያደረገ አሠራር በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን በአሁኑ ወቅት ወደ ክልል ከተሞች ተስፋፍቶ አስደናቂ ንቅናቄን ፈጥሯል።

እንደ ባሕር ዳር፣ ሐረር፣ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ጅማ እና ጅግጅጋ የመሳሰሉ የክልል ከተሞች የየራሳቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ የኮሪደር እና የውበት ልማት ሥራዎችን በስፋት ጀምረዋል።

ይህ ንቅናቄ በየከተሞቹ ያለውን የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት አቅም ከማጎልበቱም ባሻገር ለነዋሪዎች ምቹ የሆነ ዘመናዊ የከተማ አኗኗርን በተግባር እያረጋገጠ ነው።

ከተሞች በትክክል ሲያድጉ እና ሲዘምኑ ከራሳቸው አልፈው ከገጠር ጋር እጅግ ጤናማ የሆነ ትስስር እና መናበብ ይፈጥራሉ።

በመደመር የልማት አቅጣጫ ከተማ እና ገጠር እርስ በእርስ የሚፋጠጡ ጠላቶች ሳይሆኑ አንዱ ለሌላው የህልውና መሠረት የሆኑ የተቀናጁ አካላት ናቸው።

በከተሞች የሚፈጠረው የካፒታል አቅም፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ሰፊ የገበያ ዕድል በቀጥታ ወደ ገጠር በመፍሰስ የአርሶ አደሩን ሕይወት ያዘምናል።

በምላሹም የገጠሩ የግብርና ምርት ለከተማው ኢንዱስትሪ እና ማኅበረሰብ አስተማማኝ ግብዓት በመሆን የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ስትራቴጂን እውን ያደርጋል።

ይህ ዓይነቱ ጤናማ የከተማ እና የገጠር ትስስር ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለንተናዊ እና አሳታፊ የሆነ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ የሚያስችል ብቸኛው እና አስተማማኙ መንገድ ነው።

የመደመር መንግሥት እየተከተለ ያለው ይህ የከተሞች ልማት ሞዴል በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማነታቸው ከተረጋገጡ ዘመናዊ የከተማ ፕላን እሳቤዎች ጋር ፍጹም የሚጣጣም ነው።

የኢትዮጵያ የኮሪደር ልማትም ይህንኑ ሰው-ተኮር አካሄድ በመከተል ከተሞችን ለሰው ልጆች ምቹ፣ ማራኪ እና ዘላቂ የማድረግ ራዕይን በተግባር እያሳየ ይገኛል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: