Search

የአዲሱ ዓለም ደኅንነት ማዕቀፍ እና የኢትዮጵያ የማይተካ ዲጂታል እና ተቋማዊ ጉልበት

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 91

ዓለማችን እጅግ የተወሳሰበ እና ድንበር ተሻጋሪ የደኅንነት ስጋት ውስጥ በምትገኝበት በዚህ ወቅት፣ የሽብርተኝነትና የሕገ ወጥ አሠራሮች ባሕሪም ከቀደመው የታጠቁ ቡድኖች ሥልጠና ወጥቶ በዲጂታል መረቦች፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እንዲሁም በሳይበር ጥቃቶች የታገዘ ሆኗል።

በተለይም ለሽብር ተግባራት የሚሆን የገንዘብ ዝውውር በሕገ ወጥ የሐዋላ መስመሮች፣ በጥሬ ገንዘብ እና በክሪፕቶከረንሲ የሚፈስ በመሆኑ፣ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በሚደረግ ባሕላዊ የመመከት እርምጃ ብቻ ሰላምን ማስከበር አዳጋች እየሆነ መጥቷል።

ይህንን መራር እውነታ ተንተርሶ ነው እንግዲህ የብሪክስ (BRICS) ስብስብ ከአሮጌው ጥቃት ተከተል ምላሽ ወጥቶ አደጋዎችን አስቀድሞ ወደ መከላከል አቅጣጫ እንዲዞር ጥሪ ያቀረበው።

ይህንን አዲስ የደኅንነት ማዕቀፍ ስኬታማ ለማድረግ የስጋት መረጃዎችን በጋራ የመያዝ፣ የሕገ ወጥ ገንዘብ ፍሰቶችን መስመር የማድረቅ፣ የዲጂታል ፕሮፓጋንዳዎችን የመመከት እንዲሁም የድንበር ቁጥጥርን በዘመናዊ የባዮሜትሪክ ቴክኖሎጂዎች የማጠናከር የተቀናጀ ሥራ ይከናወናል።

በዚህ ዓለም አቀፋዊ የደኅንነት ማዕቀፍ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ተራ ተመልካችነት ሳይሆን አቅም ሰጪና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ነው።

ሀገራችን በአክራሪነት በተፈተነው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውስጥ እንደ አልሸባብ ያሉ አክራሪ ቡድኖችን በመመከት ረገድ ያከማቸችው ዘመናት የተሻገረ የመስክና የደኅንነት ልምድ ለብሪክስ አባላት ትልቅ ሀብት ነው።

በተለይም ኢትዮጵያ በጥሬ ገንዘብ ይደረግ የነበረውን የገንዘብ ዝውውር በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ዲጂታልና ካሽለስ አሠራር የቀየረችበት ፈጣን ሽግግር፣ በጥላ ሥር የሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጥ የሐዋላና የሽብር ፋይናንስ መረቦችን የመከታተልና የማድረቅ ሀገራዊ አቅሟን ከፍ አድርጎታል።

ከዚህ ጎን ለጎን በመከላከያ፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (INSA) እና በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ተቋማት ላይ የተደረጉት መሠረታዊ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ሪፎርሞች፣ ሀገራችን ከብሪክስ አባላት ጋር በጋራ የመረጃ ቋት፣ በሳይበር መከላከልና በቅድመ መረጃ ልውውጥ ረገድ እኩልና ተጽዕኖ ፈጣሪ አጋር ሆና እንድትሰለፍ ያደርጋታል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግሯ፣ በዘመነ የደኅንነት ሪፎርሟ እና በታሪካዊ የጸረ ሽብር ተሳትፎዋ የታገዘ ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች።

በሰለሞን ገዳ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: