ኢትዮጵያውያን በባሕር በር አጀንዳ ላይ አንዳችም መወላወል የሌለበት በፅኑ መተማመን እና በአንድነት ላይ የተገነባ ሀገራዊ የጋራ አቋም አላቸው።
ይህ ታላቅ አቋም ከተለመደው ታሪካዊ መብት ጥያቄ ወጥቶ ሲመረመር ጥልቅ የሆነ ሥነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ መሠረት ያለው ከመሆኑም በላይ፣ ከተበታተነ አስተሳሰብ ወደ አንድነት የሚያሸጋግረው የመደመር እሳቤ ህያው ማረጋገጫ ይሆናል።
ኢትዮጵያን ያለ ባሕር በር የማስቀረቱ ታሪካዊ ስህተት በዜጎች ህሊና ውስጥ የተፈጥሮ መብትን የማስከበር እና የባሕር በር ባለቤት የመሆን ጽኑ ፍላጎት እና ቁጭት ፈጥሮ ቆይቷል።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ሙሉ በሙሉ በሌሎች ሀገራት በሮች ላይ ጥገኛ መሆኗ ለፖለቲካዊ ጫና፣ ለከፍተኛ ደኅንነት ስጋት ከመሆኑ ባለፈ በየዓመቱ ለወደብ ክራይ የምታወጣው የተጋነነ ከፍያ የዜጎችን ኪስ እየጎዳ ይገኛል።
ስለሆነም የባሕር በር አጀንዳ በይፋ መነሳቱ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ውስጣቸው ሲብሰለሰል የኖረውን ስሜት እና ፍላጎት በይፋ የገለጹበት፣ የጋራ ቁስላቸውን ያከሙበት አዲስ ምዕራፍ ፈጥሯል።
የባሕር በር ጉዳይ የሐሳብ ብቻ ወይም የፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን፣ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የነገ ህልም እና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ማኅበረሰቡ በደንብ ተረድቶታል።
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው በውጭ ኃይሎች ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ጥገኛ እንዳትሆን ያላቸው ጥልቅ ስጋት እና የታላቅነት ራዕይ በአንድ ላይ አስተስስሯቸዋል።
በተበታተነ አቅም የውጭ ጫናዎችን መመከት እንደማይቻል የተረዳው ማኅበረሰቡ በባሕር በር አጀንዳ ዙሪያ በመደመር እሳቤ ሀገራዊ አቅሙን አጎልብቷል።
ይህ ጥያቄ የዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ መብቶችን መሠረት ያደረገ እና የጎረቤቶችን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ በጋራ ልማት እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚመራ ነው።
ሂደቱ ከችግር ለመሸሽ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ላቀ ሀገራዊ ከፍታ እና ቀጣናዊ መሪነት ለመሸጋገር ያለው የጋራ ህልም ውጤት ነው።
ኢትዮጵያውያን በባሕር በር አጀንዳ ላይ አንድ የሆኑት በዘመቻ ሳይሆን፣ የነገዋን ሀገር በፅኑ መሠረት ላይ ለማቆም እና በመደመር እሳቤ የታላቅነታቸውን ማህተም ለማስጠበቅ ባላቸው ጥልቅ የጋራ ፍላጎት ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: