በአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ እና የጂኦ-ስትራቴጂ የታሪክ ሂደት ውስጥ፣ የአፋር ሕዝብ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ እና በጅቡቲ መካከል የተከፋፈለ ብሔር በመሆኑ ምክንያት ለረጅም ዘመናት ለተወሳሰበ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መገለል ሲዳረግ ቆይቷል።
በተለይም ከ1983 ዓ.ም የሥርዓት ለውጥ በኋላ የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ተደራሽነት የማጨለም እና የአፋርን ሕዝብ ከታሪካዊ መሬቱ የመነጠል ሰፊ የጂኦ-ፖለቲካዊ ሤራ ተግባራዊ ሆኗል።
የአርዱፍ ትግል፡ መነጠልን የጠላው ሕዝብ ድምፅ
ዘመቻ አርዱፍ ባለ ሁለት ገጽታ ታሪካዊ ክስተት ነው። በ1985 ዓ.ም የተመሠረተው የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያን መቃወም አልነበረም፡፡ ይልቁንም በኤርትራ መገንጠል ምክንያት ሕዝቡ ለሁለት መከፈሉን በጽኑ በመቃወም፣ የአፋር ሕዝብ አንድነት እንዳይፈርስ የተደረገ የህልውና ትግል እንደሆነ መሪዎቹ በገልጽ አስቀምጠዋል።
አርዱፍ የቀይ ባሕር አፋርን ከአፋር እና ከኢትዮጵያ ነጥሎ በኃይል ለመውሰድ የተደረገውን እንቅስቃሴ ለመመከት የተቋቋመ ሕዝባዊ ኃይል ነው።
ይሁን እንጂ በ1987 ዓ.ም የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመቀናጀት በዳሎል እና አካባቢው ሰፊ ፀረ-አመፅ ወታደራዊ ዘመቻ አካሂዷል።
የዚህ ጥምር ወታደራዊ ዘመቻ ዋነኛ የጂኦ-ፖለቲካ ግብ ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ አፋሮችን ከቀይ ባሕር ዳርቻ በማራቅ ኢትዮጵያን ከባሕር በሯ ሙሉ በሙሉ መነጠል እና የኤርትራን መንግሥት የአሰብ ባለቤትነት ያለ ተቀናቃኝ ማረጋገጥ ነበር።
በዚህ ሂደት የወቅቱ የኢትዮጵያ አስተዳደር የአፋርን ሕዝብ እውነተኛ ወኪሎች በማግለል በ1988 ዓ.ም አርዱፍን በምክትል ዋና ፀሐፊነት ይመሩ የነበሩትን አቶ ሙሂያዲን መፋታህን ጨምሮ ሌሎች መሪዎችን ከጅቡቲ መንግሥት ጋር በመተባበር በማስያዝ ወደ አዲስ አበባ አሳልፈው እንዲሰጡ አድርጓል።
አስተዳደራዊ መዋቅሩንም ከነባሩ ማዕከል አውሳ ወደ በረሃማዋ ሰመራ በማዛወር የባህላዊ መሪዎችን ፖለቲካዊ አቅም አዳክሟል።
የኤርትራ መንግሥት የ35 ዓመታት ሤራ እና የአሰብ መራቆት
የኤርትራ መንግሥት ባለፉት 35 ዓመታት አሰብን እና የቀይ ባሕር አፋሮችን በተቀናጀ ስልት ከባሕር ዳርቻ ለማራቅ ሠርቷል።
የቀይ ባሕር አፋር ኢትዮጵያ ጋር ያለው የማይነጣጠል የህልውና እና የጂኦ-ፖለቲካ ትስስር ለመበጠስ የኤርትራ መንግሥት ሕዝቡን ተፈጥሯዊ የባሕር ሀብቱ ከሆነው አሰብ አግልሎታል።
የአካባቢው ነዋሪዎች የነበራቸውን የዓሣ ማስገር እና የንግድ መብት በመከልከል፣ ባህላዊ የኢኮኖሚ መዋቅራቸውን ሙሉ በሙሉ አፍርሷል።
ዛሬ ላይ አሰብ ከቀድሞው የንግድ ድምቀቷ ተነጥላ የተተወች፣ የፈረሰች እና ነዋሪዎቿ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚገኙባት የሙት ከተማ ሆናለች።
የኤርትራ መንግሥት አፋሮችን ከቀይ ባሕር ዳርቻ እያፈናቀለ ወደ በረሃማው የውስጥ ክፍል እንዲሰደዱ በማድረግ፣ አካባቢውን የማራቆት ሤራውን በተጨባጭ ፈጽሟል።
በቅርቡ ኢቢሲ ያቀረበው "የቀይ ባሕር አፋሮች" ዘጋቢ ፊልም ይህንን የተረሳ የሕዝብ እንባ አደባባይ አውጥቶታል።
በዘጋቢ ፊልሙ ላይ በግልጽ እንደታየው፣ በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኙ አፋሮች ዛሬም ድረስ ከመሠረታዊ አገልግሎቶች የተገለሉ፣ በማንነታቸው የሚሰደዱ እና ሀብታቸውን የተነጠቁ ናቸው።
ታሪካዊ መሬታቸው የውጭ ኃይሎች የጦር ሠፈር ማቋቋሚያ ሲሆን፣ እነሱ ግን በገዛ ቀያቸው የባይተዋርነት ኑሮን እየገፉ ይገኛሉ።
ይህ እውነታ አንድ ትልቅ መልእክት ያስተላልፋል፤ የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ጥያቄ የኢኮኖሚ እና የንግድ መስመር ፍላጎት ብቻ አይደለም።
ጥያቄው ከተፈጥሯዊ ወሰኑ በሤራ የተፈናቀለውን እና ለ35 ዓመታት በጭቆና ውስጥ ያለውን የተገፋ የአፋር ሕዝብን የማዳን፣ እንዲሁም በሁለት የተከፈለውን ማኅበረሰብ ፍትሐዊ መብት የማስመለስ የሞራል እና የታሪክ ግዴታ ጭምር ነው።
የአፋርን አርብቶ አደር ሕዝብ ዘለቄታዊ ሰላም እና ልማት ማረጋገጥ የሚቻለው ኢትዮጵያ ከተፈጥሯዊ የባሕር በሯ እና በባሕሩ ዳርቻ ከሚኖረው ሕዝቧ ጋር ያላትን ታሪካዊ ትስስር በማደስ ብቻ መሆኑን የዘመቻ አርዱፍ የታሪክ ሂደት እና የዛሬው የአሰብ ተጨባጭ ሁኔታ በጉልህ ያስተምረናል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: