Search

ከኃይል ማመንጨት እስከ ባሕር በር፦ ቀጣናዊ ዕድገትን ማዕከል ያደረገው ዲፕሎማሲ

ረቡዕ ነሐሴ 20, 2018 42

የኢትዮጵያ አዲሱ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ከትናንቱ የተሳሳተ ትርክት በመውጣት፣ ከውስጥ በተገነባ ጥንካሬ ብሔራዊ ጥቅሟን በዓለም አቀፍ አደባባይ በማስከበር ላይ የተመሰረተ ነው።

በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የባሕር በር ፍላጎት እና የድንበር ተሻጋሪው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ የጋራ ብልጽግና ማዕከል እና የኃይል አቅርቦት መሪ ያደረጉበት ታሪካዊ ሂደት ተፈጥሯል።

ተደጋጋሚ የውጭ ተፅዕኖዎችን እና ውስብስብ ውጣ ውረዶችን አልፎ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገራችንን የኃይል ፍላጎት ከመሸፈን አልፎ የምሥራቅ አፍሪካን የኢኮኖሚ ትስስር ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሯል።

ኢትዮጵያ እንደ ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ሱዳን ላሉ የጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ማከፋፈያ ማዕከል (East African Power Pool) ራዕይን ዕውን እያደረገች ትገኛለች።

ይህን ኃይል በስፋት ማቅረቧ ቀጣናው በኢንዱስትሪ እና በመሰረተ ልማት እንዲተሳሰር በር የከፈተ ሲሆን፣ የጎረቤት ሀገራትን የኃይል እጥረት በማቅለል የጋራ የኢኮኖሚ እድገት እንዲፋጠን አድርጓል።

በዚህም ኢትዮጵያ በቀጣናው ዘላቂ የኃይል መሪ እና አስተማማኝ የልማት አጋር መሆኗን በግልጽ አስመስክራለች።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የታሪካዊ፣ ህጋዊ፣ ጂኦግራፊያዊ እና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎችን መሰረት ያደረገ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ነው።

130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና እያደገ ያለ ግዙፍ ኢኮኖሚ የምታስተዳድር ሀገር እንደመሆኗ፣ የባሕር በር ባለቤት መሆን የህልውና ጉዳይ ሆኗል።

ይህ ፍላጎት የማንንም ሉዓላዊ ጥቅም የማይጎዳ፣ ይልቁንም የጋራ ንግድን፣ የኢኮኖሚ ትስስርን እና የድንበር ተሻጋሪ የንግድ ቀጣናዎችን የሚያጠናክር ፍትሐዊ ጥያቄ ነው።

የባሕር በር ማግኘት የኢትዮጵያን ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም ከቀጣናው ጋር በማገናኘት የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል።

ይህም በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና የተሳለጠ የንግድ ፍሰት እንዲኖር የሚያስችል ስትራቴጂካዊ የዲፕሎማሲ እርምጃ ነው።

የኢትዮጵያ "ቅድሚያ ለጎረቤት" መርህ በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር የጸና ለመሆኑ ሌላኛው ማሳያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ነው።

ባለፉት ስምንት ዓመታት 56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ያስመዘገበችው ስኬት እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት ማካፈሏ የመርሐ ግብሩን ተሻጋሪነት አሳይቷል።

ይህ ተግባር የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት ከጎርፍ፣ ከአፈር መሸርሸር እና ከድርቅ የመጠበቅ ትልቅ አካባቢያዊ ከለላ ሆኗል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ስትጠናከር እና ስትለመልም ቀጣናው አብሮ እንደሚረጋጋ እና እንደሚያብብ ማረጋገጫ ሲሆን፣ ሀገራችን በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ አህጉራዊ መሪነቷን የያዘችበት ታላቅ ሕዝባዊ ዐሻራ ነው።

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት የሚጀምረው ከውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ ነው። የሕዳሴውን ግድብ፣ የአረንጓዴ አሻራን እና የባሕር በር አጀንዳን በማስተሳሰር ኢትዮጵያን ወደ ሙሉ ልዕልናዋ በመውሰድ የምስራቅ አፍሪካ የጋራ ብልጽግና ማዕከልነቷ እውን ይሆናል።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: